የሜክሲኮ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች ኳታር ዶሃ ባለፈው ዓመት በተደረገ ጨዋታ ወቅት ጭንቅላቱ ላይ ውሃ ሲያፈስ።

የዓለም ዋንጫ 2022፡ የበረሃ ላይ ስታዲየሞችን ሚያቀዘቅዙ ድንቅ መንገዶች

የባሕረ ሰላጤዋ አገር ኳታር የ2022 የዓለም ዋንጫን እንድታስተናግድ ስትመረጥ ጥያቄዎች ተነስተውባት ነበር። አገሪቱ ካላት የሰብዓዊ መብት አያያዝ አንስቶ፣ ከ40 ዲግሪ ሴሊሺየስ በሚበልጠው ሙቀቷ ተጫዋቾች እና ተመልካቾች እንዴት በውድድሩ ላይ ሊሳተፉ ይችላሉ የሚሉት ዋናዎቹ ናቸው።

ውድድሩን ወደ ቀዝቃዛ ወቅት ማሸጋገር አንድ አማራጭ ነበር። ባለፀጋዋ በረሃማ አገር ግን፤ ዘመን አፈራሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም በየትኛውም ወቅት ግዙፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን ማካሄድ እንደሚቻል ለማሳየት ቆርጣለች። የኳታር ዜጋ የሆነው እግር ኳስ ተጫዋች ሃጃር ሳሌህ ሙቀት እና ወበቁ በመካከለኛው ምሥራቅ እግር ኳስ መጫወትን ፈታኝ ያደርጉታል ይላል።

ኳታር በከባቢ አየር ላይ ጉዳት ሳይደርስ፣ ለተጫዋቾች እና ተመልካቾች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ምን እያደረገች ነው?

በአል ጃኑብ ስታዲየም ሞቃት አየርን የሚያመለክቱ ቀይ ቀስቶች

በሜዳው ላይ እና በተመልካቾች መቀመጫ አካባቢ ቀዝቀዝ ያለ የአየር ሁኔታን ለመጠበቅ ፈጠራ የታከለበት መፍትሄ አስፈልጓል። በኳታር ይህ እንዴት ሆነ? እንመለከተው!

ጨዋታ በሚካሄድባቸው ቀናት 40 ሺህ ሰዎች በስታዲየም ይገኛሉ። ተመልካቾቹ እራሳቸው የሙቀት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ።

የኳታር ሙቀት እና በስታዲየም የሚታደሙት ተመልካቾች የሚፈጥሩት ወበቅ ተቆጣጥሮ መቹ ሁኔታን ለመፍጠር ውጤታማ የሆነ የማቀዝቀዣ ሥርዓት ያስፈልጋል።

በስታዲየሞች ውስጥ ባሉ በእያንዳንዱ መቀመጫ ስር የሚገጠሙት የአየር ማቀዝቀዣዎች ተመልካቾች ቀዝቃዛ አየር እንዲያገኙ ያስችላሉ።

እንደ የሻውር ውሃ መፍሰሻ ቅርጽ ያላቸው አነስተኛ ቁሶች ወደ ተመልካቾቹ የተስተካከለ አየር በመርጨት የስታዲየሙን ዙሪያ ይሸፍኑታል።

ይህም ምቾት በማይነሳ ሁኔታ ከተመልካቾች አናት ላይ በስሱ አየር ስለሚለቅ የአየር ፍሰት ይኖራል።

ይህ ለተመልካቾች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፣ በሜዳ ላይ ላሉት ተጫዎቾችስ?

በዘመናዊ እግር ኳስ አንድ ተጫዋች በአንድ ግጥሚያ ላይ 10 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ርቀት በመሮጥ፣ 3 ሊትር የሚደርስ ላብ ያወጣል። ስለዚህ ተጫዋቾች ቀዝቃዛ አየር ማግኘት አለባቸው፤ የሰወነታቸው ፈሳሽ መሟጠጥ የለበትም።

የአል ጃኑብ ስታዲየም ኳታር ሜዳ እና የተመልካች ቦታ ላይ ያለው ቀዝቃዛ አየር በሰማያዊ የሚያሳይ ግራፊክስታ

በሞቃታማዋ ኳታር ላብ ተኖ ለመውጠት ይቸገራል፣ በዚህም ሰውነት ከልክ በላይ ሞቆ በጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

ስለዚህ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ መጠናቸው ከፍ ያለ የቀዝቃዛ አየር ቱቦዎች በስታዲየሙ ዙሪያ ቀዝቃዛ አየር በመርጨት በሜዳው ላይ ላሉ ተጫዎቾች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራሉ።

በኳታር የአየር ማቀዝቀዣ ሥርዓት ግንባታ ላይ ተሳታፊ የሆኑት ዶ/ር ሳዑድ አብዱል ጋኒ እንደሚሉት፣ የቀዝቃዛ አየር ማመንጫዎቹ አቀማመጥ እና አጠቃላይ አሰራራቸው ተፈጥሯዊ ሁኔታን እንዲከተሉ በመደረጋቸው ተጨዋቾችን በምንም መልኩ አያውኩም።

ይህ ስርዓት በሜዳው እና ከተመልካቾች መቀመጫ ሁለት መሬት ከፍታ ድረስ ያቀዘቅዛል እንጂ ሙሉ በረሃማውን ከባቢ አያጠቃልልም። ቀጥሎስ ምን ይሆናል?

ቀዝቀዝ ያለው አየር ቀስ በቀስ እየሞቀ ሲሄድ፤ በስታዲየሙ መካከለኛ ክፍል ላይ በተገጠሙት መሳሪያዎች የሞቀው አየር እየተሳበ ወደ ውጪ እንዲወጣ ይደረጋል።

ከዚያም ተጣርቶ እና ቀዝቅዞ ተመልሶ በስታዲየሙ ዙሪያ ባለው የማቀዝቀዣ ሥርዓት ውስጥ ዳግም ይለቀቃል።

ቀዝቃዛው ውሃ ሙቁን አየር ከመጠጠው በኋላ 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ሚገኘው እና 40 ሺህ ሊትር ውሃ የመያዝ አቅም ወዳለው የማጠራቀሚያ ገንዳ በመሄድ ለቀጣዩ ቀን ጨዋታ ዝግጁ ይሆናል።

የስታዲየሙን ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ሚያሳይ ግራፊክስ

ይህ አጠቃላዩ የማቀዝቀዣ ሥርዓት በቅርቡ ከዋና ከተማ ዶሃ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከተገነባው ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሚፈልገውን ኃይል ያገኛል።

ዶ/ር 'ኩል'

ይህንን የአየር ማቀዝቀዣ አጠቃላይ ሥርዓት የቀረጹት ዶ/ር ሳዑድ አብዱል ጋህኒ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኳታር በዚህ ውድድር ስሟን ተክላ ማለፍ ትፈልጋለች። ይህም ሥርዓት ውድድሩ አብቅቶ ተጫዋቾቹ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላም የተዘረጋው ሥርዓቱ አገሪቱን እንዲያገለግል ፍላጎት አለ።

ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሰው ምቾትን የሚፈጥር ከባቢን ለማዘጋጀት እና “በሙቀት ውስጥ ምቾት” ይሰጣል ያሉትን ይህንን ሥርዓት ለመገንባት፣ ዓመታት የወሰደ ሰፊ ጥናት እንደተካሄደ ተናግረዋል። እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 በኳታር በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከተሳተፉ አትሌቶች እና ተመልካቾች ጋር ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ ይህም በዓለም ዋንጫ ለሚሳተፉ ተመልካቾች እና ተጨዋቾች የተሻለ ሁኔታ ለማዘጋጀት ረድቷል።

የተጫዋች ምልከታ

ከ11 ዓመቷ ጀምሮ እግር ኳስ ስትጫወት ካደገችውና በኳታር የሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተከላካይ የሆነችውን ሃጃር ሳሌህን ቢቢሲ አናግሯት ነበር። ተጫዋቿ በሞቃታማ ሁኔታዎች ውስጥ መጫወት የሚጠይቀውን ነገር በሙሉ ጠንቅቃ ታውቃለች። እርሷ እንደምትለው ሙቀትና ወበቅ ከባድ ፈተናዎች ናቸው።

በሙቀት ውስጥ መጫወትን ለምደነዋል፤ ነገር ነግር ግን በሙቀት እና ወበቅ ውስጥ መጫወት በጣም ከባድ ነው። ሃጃር ሳሌህ

ሃጃር አዲሱ የማቀዝቀዣ ሥርዓት በተገነባላቸው ኻሊፋ እና ኤጁኬሽናል ሲቲ ስታዲየሞች ውስጥ በመጫወት ያለውን ለውጥ ለማየት ዕድሉን አግኝታ ነበር።

የተዘረጋው የማቀዝቀዣ ሥርዓት፣ በተለይ በኳታር ከፍተኛ ሙቀት በሚኖርበት የሰኔ ወር ላይ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ትናገራለች።

የማቀዝቀዣው ሥርዓት ዘላቂ ነው?

የኤሌክትሪክ ኃይሉ ከፀሐይ ብርሃን የሚመነጭ መሆኑን በመጥቀስ፣ በስታዲየሞቹ ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የአየር ብክለት እንደማይከሰት የኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ አዘጋጆች ተናግረዋል።

ነገር ግን አጠቃላዩን የዓለም ዋንጫ ውድድር ከበካይ ጋዞች የጸዳ ለማድረግ ያለው ዕቅድ ግን ደፈር ያለ ምኞት ይመስላል።

ስታዲየሞቹን በሚገነቡበት ጊዜ የተፈጠረው የበካይ ጋዝ ልቀት 90 በመቶ የሚሆነውን የቦታዎቹን አጠቃላይ የካርበን መጠን የሚይዝ እና 800 ሺህ ቶን የሚገመት የሙቀት አማቂ ጋዞች ወደ ከባቢ አየር ይለቃሉ። ይህ ማለት ደግሞ የአሜሪካ የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ የልቀት ስሌት እንደሚለው በዓለም ዙሪያ 80 ሺህ ጊዜ አንድ የመንገደኞችን መኪና ከማሽከርከር ጋር እኩል ነው።

ከስታዲየሞቹ ባሻገር ደግሞ ወደ ኳታር የዓለም ዋንጫ የሚደረጉ የደጋፊዎች የአውሮፕላን ጉዞን ጨምሮ መጓጓዣዎች ተጽእኖ አላቸው።

ፊፋ እንደሚለው ኳታር ውስጥ የዓለም ዋንጫ ውድድር በሚካሄድባቸው ስታዲየሞች መካከል ያለው ርቀት ቅርብ በመሆኑ፣ ከአንድ የውድድር ስፍራ ወደ ሌላ የሚደረጉት ጉዞዎች አጭር ስለሚሆኑ እአአ 2018 በሩሲያ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ከነበረው የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን ይቀንሳል።

ኳታር ውድድሩን ለማዘጋጀት በተመረጠችበት ወቅት በገባችው ከባቢ አየርን የመጠበቅ ቃል ኪዳን መሠረት፣ ለውድድሩ አጠቃላይ ዝግጅትና ሂደት የሚመነጨውን ካርቦን ዳይኦክሰይድ (CO2) በማካካስ ላይ አትኩራለች።

እስካሁን ይህንን ግብ እንዴት እንደሚያሳኩት ግልጽ አይደለም። ፊፋ ግን በዓለም ዋንጫ የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ ለማካካስ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀመ መሆኑን ይገልጻል። ይህም ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂ፣ ታዳሽ ኃይል እና ችግኝ መተከልን እንደሚያጠቃልል ነው። ሆኖም ግን የመጨረሻው የፕሮጀክቶች ምርጫ እስካሁን አልተረጋገጠም።

እንዲህ አይነት አሳራሮች የተበከለ አየርን በማስወገድ ውጤታማ ለመሆን አስርት ዓመታት ሊፈጁ ይችላል። ቢቢሲ በቅርቡ ያደረገው ጥናት፣ የአየር ብክለትን ለማካካስ በሚል የተተከሉ ዛፎች ከወረቅ ባለፈ መሬት ላይ እንደሌሉ አመላክቷል።

እናም ኳታር የተበከለ አየር መቆጣጠርን በተመለከተ ያስቀመጠቻቸው አረንጓዴ ግቦችን ማሳካት፣ አለማሳካቷን ለማረጋገጥ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም።

በሌላ በኩል ደግሞ ኳታር 30 ሺህ የውጭ አገራት ዜጎች በተሳተፉበት የስታዲየሞች ግንባት ላይ በርካታ ሠራተኞች የሞት እና ከባድ የአካል ጉዳትን ጨምሮ ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት ደርሷል በሚል የሚቀርብባታን ትችት ታስተባብላለች። በተጨማሪም ሠራተኞቹ በግዳጅ የጉልበት ሥራ፣ በማይመች የሥራ እና የተጨናነቀ መኖሪያ ሁኔታ እንዲሁም ደሞዝ ባለመክፈል እና ፓስፖርታቸውን በመቀማት አገሪቱ እየተወቀሰች ትገኛለች።

ሆኖም የኳታር መንግሥት ከሚቀርቡበት ክሶች በተቃራኒ ከእአአ 2017 ጀምሮ ከውጭ አገራት የሚመጡ ሠራተኞችን ከኃይለኛ ሙቀት ለመጠበቅ የሚያስችል እርምጃዎችን መውሰዱን፣ ውስን የሥራ ሰዓት እና የተሻለ የመኖሪያ ስፍራን ማመቻቸቱን ገልጿል። ሆኖም እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 ብቻ ከዓለም ዋንጫ ዝግጅት ግንባታዎቸ ጋር በተያያዘ 50 ሰዎች ሲሞቱ፣ 500 የሚሆኑት ድግሞ ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የዓለም ሥራ ድርጀት ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ይህም በረሃማዋ አገር ላይ ከውድድሩ ጋር ተያይዞ የሚቀርብባት ጥያቄ ነው።