ዶ/ር 'ኩል'
ይህንን የአየር ማቀዝቀዣ አጠቃላይ ሥርዓት የቀረጹት ዶ/ር ሳዑድ አብዱል ጋህኒ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኳታር በዚህ ውድድር ስሟን ተክላ ማለፍ ትፈልጋለች። ይህም ሥርዓት ውድድሩ አብቅቶ ተጫዋቾቹ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላም የተዘረጋው ሥርዓቱ አገሪቱን እንዲያገለግል ፍላጎት አለ።
ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሰው ምቾትን የሚፈጥር ከባቢን ለማዘጋጀት እና “በሙቀት ውስጥ ምቾት” ይሰጣል ያሉትን ይህንን ሥርዓት ለመገንባት፣ ዓመታት የወሰደ ሰፊ ጥናት እንደተካሄደ ተናግረዋል። እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 በኳታር በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከተሳተፉ አትሌቶች እና ተመልካቾች ጋር ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ ይህም በዓለም ዋንጫ ለሚሳተፉ ተመልካቾች እና ተጨዋቾች የተሻለ ሁኔታ ለማዘጋጀት ረድቷል።
የተጫዋች ምልከታ
ከ11 ዓመቷ ጀምሮ እግር ኳስ ስትጫወት ካደገችውና በኳታር የሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተከላካይ የሆነችውን ሃጃር ሳሌህን ቢቢሲ አናግሯት ነበር። ተጫዋቿ በሞቃታማ ሁኔታዎች ውስጥ መጫወት የሚጠይቀውን ነገር በሙሉ ጠንቅቃ ታውቃለች። እርሷ እንደምትለው ሙቀትና ወበቅ ከባድ ፈተናዎች ናቸው።
በሙቀት ውስጥ መጫወትን ለምደነዋል፤ ነገር ነግር ግን በሙቀት እና ወበቅ ውስጥ መጫወት በጣም ከባድ ነው። ሃጃር ሳሌህ
ሃጃር አዲሱ የማቀዝቀዣ ሥርዓት በተገነባላቸው ኻሊፋ እና ኤጁኬሽናል ሲቲ ስታዲየሞች ውስጥ በመጫወት ያለውን ለውጥ ለማየት ዕድሉን አግኝታ ነበር።
የተዘረጋው የማቀዝቀዣ ሥርዓት፣ በተለይ በኳታር ከፍተኛ ሙቀት በሚኖርበት የሰኔ ወር ላይ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ትናገራለች።
የማቀዝቀዣው ሥርዓት ዘላቂ ነው?
የኤሌክትሪክ ኃይሉ ከፀሐይ ብርሃን የሚመነጭ መሆኑን በመጥቀስ፣ በስታዲየሞቹ ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የአየር ብክለት እንደማይከሰት የኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ አዘጋጆች ተናግረዋል።
ነገር ግን አጠቃላዩን የዓለም ዋንጫ ውድድር ከበካይ ጋዞች የጸዳ ለማድረግ ያለው ዕቅድ ግን ደፈር ያለ ምኞት ይመስላል።
ስታዲየሞቹን በሚገነቡበት ጊዜ የተፈጠረው የበካይ ጋዝ ልቀት 90 በመቶ የሚሆነውን የቦታዎቹን አጠቃላይ የካርበን መጠን የሚይዝ እና 800 ሺህ ቶን የሚገመት የሙቀት አማቂ ጋዞች ወደ ከባቢ አየር ይለቃሉ። ይህ ማለት ደግሞ የአሜሪካ የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ የልቀት ስሌት እንደሚለው በዓለም ዙሪያ 80 ሺህ ጊዜ አንድ የመንገደኞችን መኪና ከማሽከርከር ጋር እኩል ነው።
ከስታዲየሞቹ ባሻገር ደግሞ ወደ ኳታር የዓለም ዋንጫ የሚደረጉ የደጋፊዎች የአውሮፕላን ጉዞን ጨምሮ መጓጓዣዎች ተጽእኖ አላቸው።
ፊፋ እንደሚለው ኳታር ውስጥ የዓለም ዋንጫ ውድድር በሚካሄድባቸው ስታዲየሞች መካከል ያለው ርቀት ቅርብ በመሆኑ፣ ከአንድ የውድድር ስፍራ ወደ ሌላ የሚደረጉት ጉዞዎች አጭር ስለሚሆኑ እአአ 2018 በሩሲያ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ከነበረው የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን ይቀንሳል።
ኳታር ውድድሩን ለማዘጋጀት በተመረጠችበት ወቅት በገባችው ከባቢ አየርን የመጠበቅ ቃል ኪዳን መሠረት፣ ለውድድሩ አጠቃላይ ዝግጅትና ሂደት የሚመነጨውን ካርቦን ዳይኦክሰይድ (CO2) በማካካስ ላይ አትኩራለች።
እስካሁን ይህንን ግብ እንዴት እንደሚያሳኩት ግልጽ አይደለም። ፊፋ ግን በዓለም ዋንጫ የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ ለማካካስ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀመ መሆኑን ይገልጻል። ይህም ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂ፣ ታዳሽ ኃይል እና ችግኝ መተከልን እንደሚያጠቃልል ነው። ሆኖም ግን የመጨረሻው የፕሮጀክቶች ምርጫ እስካሁን አልተረጋገጠም።
እንዲህ አይነት አሳራሮች የተበከለ አየርን በማስወገድ ውጤታማ ለመሆን አስርት ዓመታት ሊፈጁ ይችላል። ቢቢሲ በቅርቡ ያደረገው ጥናት፣ የአየር ብክለትን ለማካካስ በሚል የተተከሉ ዛፎች ከወረቅ ባለፈ መሬት ላይ እንደሌሉ አመላክቷል።
እናም ኳታር የተበከለ አየር መቆጣጠርን በተመለከተ ያስቀመጠቻቸው አረንጓዴ ግቦችን ማሳካት፣ አለማሳካቷን ለማረጋገጥ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም።
በሌላ በኩል ደግሞ ኳታር 30 ሺህ የውጭ አገራት ዜጎች በተሳተፉበት የስታዲየሞች ግንባት ላይ በርካታ ሠራተኞች የሞት እና ከባድ የአካል ጉዳትን ጨምሮ ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት ደርሷል በሚል የሚቀርብባታን ትችት ታስተባብላለች። በተጨማሪም ሠራተኞቹ በግዳጅ የጉልበት ሥራ፣ በማይመች የሥራ እና የተጨናነቀ መኖሪያ ሁኔታ እንዲሁም ደሞዝ ባለመክፈል እና ፓስፖርታቸውን በመቀማት አገሪቱ እየተወቀሰች ትገኛለች።
ሆኖም የኳታር መንግሥት ከሚቀርቡበት ክሶች በተቃራኒ ከእአአ 2017 ጀምሮ ከውጭ አገራት የሚመጡ ሠራተኞችን ከኃይለኛ ሙቀት ለመጠበቅ የሚያስችል እርምጃዎችን መውሰዱን፣ ውስን የሥራ ሰዓት እና የተሻለ የመኖሪያ ስፍራን ማመቻቸቱን ገልጿል። ሆኖም እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 ብቻ ከዓለም ዋንጫ ዝግጅት ግንባታዎቸ ጋር በተያያዘ 50 ሰዎች ሲሞቱ፣ 500 የሚሆኑት ድግሞ ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የዓለም ሥራ ድርጀት ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ይህም በረሃማዋ አገር ላይ ከውድድሩ ጋር ተያይዞ የሚቀርብባት ጥያቄ ነው።