የቢቢሲ የ2023 100 ሴቶች፡ በዚህ ዓመት ዝርዝር ውስጥ እነማን ተካተቱ?
ቢቢሲ የ2023 በመላው ዓለም ተጽእኖ ፈጣሪ እና ሌሎችን በማነሳሳት የመረጣቸው 100 ሴቶች ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
ከእነዚህ መካከል የሰብዓዊ መብቶች ጠበቃዋ አማል ክሉኒ፣ የሆሊውድ ኮከቧ አሜሪካ ፌሬራ፣ የሴቶች መብት ተሟጋቿ ግሎሪያ ስቴይኔም፣ የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ፣ የመዋቢያ ምርቶች ንግድ ባለቤት ሁዳ ካታን እና የባለን ዶር አሸናፊ እግር ኳስ ተጫዋች አይታና ቦንማቲ ይገኙበታል።
እንደ ከፍተኛ ሙቀት፣ የሰደድ እሳት፣ ጎርፍ እና ሌሎች ተፈጥሯዊ አደጋዎች ትኩረትን ይዘው በቆዩበት ዓመት፤ ከተመረጡት ሴቶች መካከል በማኅብረሰባቸው ላይ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ሲረዱ የቆዩም ይገኙበታል።
ከቢቢሲ 100 ሴቶች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ፈረ ቀዳጅ የሆኑትን 28 ሴቶች የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ 'ኮፕ28' ከመካሄዱ በፊት ይፋ እናደርጋለን።
የስም ዝርዝሩ በደረጃ የተቀመጠ አይደለም
ባሕል እና ትምህርት
ክላራ ኤልዛቤት ፍራጎሶ ኡጋርቴ , ሜክሲኮ
የከባድ መኪና ሹፌር
የከባድ መኪና አሽከርካሪዋ በወንዶች የበላይነት በተያዘው የሹፍርና ሙያ ለ17 ዓመታት ሠርታለች። በሥራዋ በሜክሲኮ አውራ ጎዳናዎች እና አደገኛ በሚባሉ የአገሪቱ መንገዶችም ተጉዛለች።
በዱራጎ ነው የተወለደችው። በ17 ዓመቷ አግብታለች። አራት ልጆች እና ሰባት የልጅ ልጆች አሏት።
በሜክሲኮ እና በአሜሪካ መካከል ሸቀጦችን በማዘዋወር ነው ሕይወቷን ያሳለፈችው።
ወጣት አሽከርካሪዎችን ታሠለጥናለች። በከባድ መኪና ማሽከርከር ዘርፍ የፆታ እኩልነት እንዲሰፍን ሴቶች ወደ ሙያው እንዲገቡም ታበረታታለች።
ቺላ ኩማሪ በርማን , ዩኬ
አርቲስት
በሕትመት፣ በሥዕል፣ በቅርጽ እና በፊልም ሥራዎች ትታወቃለች። በሥራዎቿን ፆታ፣ ባህል እና ማንነት የሚወከሉበትን ሁኔታ በማንሳት መወያያ እንዲሆኑ ታውለዋለች።
በዩናይትድ ኪንግደም ያለ ከ1879 (እአአ) ጀምሮ የዘለቀ የመብራት ትዕይንት 'ብላክፑል ኢሉምኔሽንስ' ላይ ሥራዎቿ ታይተዋል። 'ሎይንስ ኢን ላቭ ዊዝ ላይት' በሚል ነው ሥራዋን ያቀረበችው። ይህም ቤተሰቦቿ በነበራቸው የአይስክሪም ንግድ ላይ የተመረኮዘ ሥራ ነበር።
በ2020 ቺላ 'ብሬቭ ኒው ዎርልድ' መነሻ አድርጋ ከሕንድ ንግርት ጋር በተያያዘ ስለ ሴቶች ኃያልነት የሚያወሳ ሥራ አቅርባለች።
ባለፈው ዓመት የኤምቢኢ ሽልማትን አግኝታለች።
ማሪዬታ ሞያሴቪች, ሞንቴኔግሮ
የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች
ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ሁለቴ ስትሮክ ገጥሟታል። ይህም ሕይወቷን ለውጦታል።
አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫናው እንዳለ ሆኖ ከወጣቶች ጋር ከመሥራት አላገዳትም። የወጣቶች አማካሪ እና የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች ናት።
የአእምሮ ጤና እክል ጋር በተያያዘ ያሉ አመለካከቶችን ለመለወጥ ድምጿን ታሰማለች።
ላይፍ ዊዝ ዲሴቢሊቲ በሚል ወርክሾች አዘጋጅታለች። ይህም ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት ያለውን መድልዎ ለመረዳት የሞከረችበት ነው።
በዓለም ዙሪያ የሕብረተስበ ጤና ላይ ያተኮረው ዋንኒውሮሎጂ የተባለው እንቅስቃሴ አምባሳደር ናት።
ሻይርቡ ሳጊይንቤቫ, ኪርጊዝታን
የስፌት ሱቅ ባለቤት
በካንሰር አራተኛ ደረጃ ሕክምና ስትከታተል ቆይታለች። ለመድኃኒት መክፈል ቀላል አልነበረም። አሁን እያገገመች ነው።
ከአራት የካንሰር ሕሙማን ጋር በመሆን 'ፎር ላይፍ' የተባለ የስፌት ሱቅ ከፍተዋል። ጌጣጌጦች በመጠቀም ቦርሳ እየሠሩ ገቢውን ለካንሰር ሕሙማን ሕክምና ያውላሉ።
ከ33 ሺህ በላይ ዶላር እስካሁን ማሰባሰብ ችለዋል። 34 ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሴቶችን የሕክምና ወጪ ሸፍነዋል።
ከሕክምና ማዕከል ርቀው ያሉ ሕሙማንን ማገዝ አስፈላጊነቱን በመረዳት ለትርፍ ያልተቋቋመ የማረፊያ ቤት ከፍታለች።
ዳሪያ ሴሬንኮ, ሩሲያ
ገጣሚ
ፀሐፊ እና የፖለቲካ አንቂ ዳሪያ፣ ሩሲያ በዩክሬን የፈጸመችውን ወረራ ከሚቃወሙ የፌምኒስት ቡድኖች አንዱ ውስጥ ትገኛለች።
በሩሲያ ስላለው ወሲባዊ ጥቃት ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ጽፋለች። ሁለት የፌምኒስትና ፀረ ጦርነት መጻሕፍት አሏት።
ኳይት ፒኬት' የተሰኘ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ስብስብ ውስጥ አለች። ሰዎች የተሻለ እንዲያደርጉ የሚያሳስቡ ጽሑዎች በመልበስ ንቅናቄ ታደርጋለች።
ሩሲያ ዩክሬንን ከመውረሯ ከሁለት ሳምንት በፊት ዳሪያ ታስራ ነበር። 'ጽንፍ የወጣ' መልዕክት በማስተላለፍ ነበር የታሰረችው። አሁን ወደ ጆርጂያ ተሰዳለች። ሩሲያ 'የውጭ ኃይል' ብላ ፈርጃታለች።
ሳጋሪካ ስሪራም, ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ
አስተማሪ እና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች
ታዳጊዋ ሳግሪካ ስሪራም የአየር ንብረት ለውጥ ትምህርት በየትምህርት ቤቱ መስጠት ግዴታ እንዲሆን ትታገላለች።
የኮዲንግ ችሎታዋን በመጠቀም በበይነ መረብ 'ኪድስ4ኤቤተርወርልድ' የሚል ንቅናቄ ታደርጋለች። ልጆች ስለዓለም እንዲያውቁ እና ማኅበረሰባቸውን በዘላቂነት እንዲደግፉ ነው የምትሠራው።
በበይረ መረብ እና በአካልም የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ ታደርጋለች። ልጆች እንዴት አካባቢያቸው ላይ አወንታዊ ተጽዕኖ ማሳደር እንደሚችሉም ታስተምራለች።
በዱባይ ከፍተኛ ውጤት የምታመጣ ተማሪ ናት። በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መብት አማካሪ ኮሚቴ ውስጥ አባል ስትሆን፣ ስለ አካባቢ መብት ታማክራለች።
አሁን ጊዜው የማስፈራራት ሳይሆን የሥራ ነው። ሁሉም ልጅ ስለ ዘላቂ ኑሮ ተምሮ በዓለም ለውጥ እንዲታይ መሪ መሆን አለበት።
ሳጋሪካ ስሪራም
ኬራ ሸርውድ-ኦሬጋን, ኒው ዚላንድ
የቀደምት ማኅበረሰብ እና የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች
በኒው ዚላድ የሚገኘው ቀደምት ማኅበረሰብ ቴ ዋፖናሙ ተወላጅ ስትሆን ለቀደምት ማኅበረሰብ እና ለአካል ጉዳተኞች መብት ትከራከራለች።
በአካባቢ ጥበቃ ፍትሕ እንዲሁም በማኅበረሰባዊ ፍትሕ የሚታወቅ አክቲቬት የተባለ ተቋም አጋር መሥራች ናት።
በማሮይ ማኅበረሰብ የመሬት ጥበቃ እና የአያት ቅድመ አያት ባህል ላይ በተመሠረተ መንገድ ነው የምትሠራው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስለ አየር ንብረት ለውጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲነገር ይህ ባህል ተዘንግቶ ነበር።
ከሚኒስትሮች እና ባለሥልጣናት ጋር እንዲሁም ከሲቪል ማኅበራት ጋር አብራ ትሠራለች። የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለማኅበረሰቧ ለማሳወቅ ነው የምትሠራው። የቀደምት ማኅበረሰቦች መብት እንዲከበር፣ አካል ጉዳተኞች የአየር ንብረት ለውጥ ውይይት አካል እንዲሆኑም ትሠራለች።
አክራሪ አካሄድን ትተን ቦታችንን እያገኘን ነው። ከማኅበረሰቡ ጋር ነው የምንመራው። ውጤታማ እየሆነም ነው። የቀደምት ማኅበረሰቦች ሉዓላዊነት ለአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ መፍትሄ እንደሆነ ብዙ ሰው እያወቀ ነው።
ኬራ ሸርውድ-ኦሬጋን
ኢሲ ቦባሳ, ጋና
ዓሳ ነጋዴ
በጋና ፉቬሜ መንደር ነው ኢሲ ቦባሳ የተወደችው። የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት አይታዋለች።
የባሕር ከፍታ ሲጨምር እና መሬታቸው በውሃ ሲሸፈን ከባለቤቷ እና ከአምስት ልጆቿ ጋር በመሆን ተሰደዋል።
በመንደሯ ዓሳ በመሸጥ ቀዳሚ ናት። በአካባቢው የደረሰው ጉዳት ገቢያቸው ላይ ጫና ስላሳደረ ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር በመሆን ዓሳ አስጋሪ ሴቶችን የሚደግፍ ማኅበር መሥርተዋል።
ማኅበሩ አሁን 100 አባላት አሉት። በንግዱ ያሉ ሴቶች ስለሚገጥማቸው መሰናክል ለመወያየት በየሳምንቱ ይገናኛሉ። ድጋፍ ለሚፈልጉ ቤተሰቦችም ገንዘብ ይሰጣሉ።
የማዕበል ሞገድ በመጣ ቁጥር እንጨነቃለን። ሞት ለእኛና ለቀጣዩም ትውልድ እየመጣ ነው።
ኢሲ ቦባሳ
ፓውሊና ቺዚያኔ, ሞዛምቢክ
ፀሐፊ
ባላድ ኦፍ ላቭ ኢን ዘ ዊንድ' በ1990ዎቹ የተጻፈ የመጀመሪያው መጽሐፏ ነው። በሞዛምቢክ ልቦለድ በማሳተም የመጀመሪያዋ ሴት ናት።
በዋና ከተማዋ ማፑቶ ነው ያደገችው። በፖርቹጋል የካቶሊክ ትምህርት ቤት ተምራለች። በኤድዋርዶ ሞንዳልን ዩኒቨርስቲ ቋንቋ ብትማርም አልተመረቀችም።
ሥራዋ በእንግሊዝኛ፣ በጀርመንኛ፣ በስፓኒሽ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። 'ዘ ፈርስት ዋይፍ፡ ኤ ቴል ኦፍ ፖሊጋሚ' በተሰኘው መጽሐፏ የሆዜ ክራቫሪኒሀ ሽልማትን አግኝታለች።
የካሞስ ሽልማትን ደግሞ ያገኘችው በቅርቡ ነው። ይህም በፖርቹጋል ትልቁ ሽልማት ነው።
ሆሳይ አህማድዛይ, አፍጋኒስታን
የቴሌቪዥን አቅራቢ
ታሊባን አፍጋኒስታንን በ2021 በድጋሚ ሲይዝ ሆሳይ አህማድዛይ የቴሌቪዥን አቅራቢ ከነበሩ ጥቂት ሴቶች መካከል ናት።
በሻምሻድ ቴሌቪዥን አቅራቢ ሆና ቀጥላለች። ሴቶች በመገናኛ ብዙኃን መሰናዶ ሲያቀርቡ ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ነው።
በርካታ የታሊባን አመራሮችን ቃለ ምልልስ አድርጋቸዋለች። ሆኖም ግን ድርጊታቸውን በተመለከተ መጠየቅ የምትችላቸው ነገሮች በጣም ውስኑ ናቸው።
የተማረችው ሕግ እና ፖለቲካ ሳይንስ ሲሆን፣ በመገናኛ ብዙኃን ለሰባት ዓመታት ሠርታለች። በታሊባን ገደብ የተጣለበት የሴቶች ትምህርት ዋነኛ ትኩረቷ ነው።
አፍሮዜ-ኑማ, ፓኪስታን
እረኛ
አፍሮዜ-ኑማ ለሦስት አሥርታት ያህል ፍየሎች እና በጎች ጠብቃለች። ከዋክሂ ማኅበረሰብ የመጨረሻዎቹ እረኞች አንዷ ናት።
ሙያውን ከእናቷ እና ከአያቷ ነው የተማረችው። በፓኪስታን እየጠፋ ያለው እና ዘመናት ያስቆጠረው ሙያ ባለቤት ናት።
እረኞቹ በየዓመቱ ከባሕር ወለል በላይ 4800 ሜትር ከፍታ ከብቶቻቸውን ይዘው ይጓዛሉ። የእንስሳት ተዋጽኦ በማዘጋጀትም ለገበያ ያቀርባሉ።
ገቢያቸው ለመንደሩም ተርፏል። ልጆቻቸውንም ማስተማር ችለዋል። አፍሮዜ-ኑማ በማኅበረሰቡ ጫማ ያላት የመጀመሪያዋ ሴት መሆኗን ታስታውሳለች።
ናታሊያ ኢድሪሶቫ, ታጂኪስታን
የአረንጓዴ ኃይል አማካሪ
በታጂኪስታን ገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች ከእንጨትም ይሁን ከኤሌክትሪክ የኃይል አቅርቦት ለማግኘት ይቸገራሉ። የአካባቢ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ አስተባባሪዋ ናታሊያ፣ ከባቢ አየር ላይ የተመረኮዙ መፍትሄዎችን ትፈልጋለች። ሴቶችን ስለ ተፈጥሯዊ የኃይል ምንጮች እና ስለ ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች ታስተምራለች።
ከማሠልጠን ጎን ለጎን ኃይል ቆጣቢ መሣሪያዎችንም በተቋሟ ሥር ታከፋፍላለች። በፀሐይ የሚሠሩ ማብሰያዎች ይገኙበታል። እነዚህም ሴቶች ጊዜ እንዲቆጥቡ የሚያስችሉ፣ የፆታ ልዩነትን የሚያጠቡ እና አካባቢን የማይበክሉ አማራጮች ናቸው።
የአየር ንብረት ለውጥ በተለይም አካል ጉዳተኞች ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ በተመለከተ ሥልጠና ትሰጣለች። ድምጻቸው በፖለቲካዊ ውይይቶች እንዲሰማም ትሠራለች።
በመላው ዓለም ያሉ አስከፊ ክስተቶች ከተፈጥሮ ለሰዎች የተላኩ ማስጠንቀቂያዎች ናቸው። በችላ ባይነት ተፈጥሮን መበዝበዝ መዘዝ ያመጣል።
ናታሊያ ኢድሪሶቫ
ሱዛኔ ኤቲ, አውስትራሊያ
የዘላቂ ቱሪዝም ባለሙያ
የቱሪዝም ዘርፍ ዘላቂነት ያለው የወደፊት ጉዞ እንዲኖረው ነው ሱዛኔ የምትሠራው።
ኢንተርፒድ ትራቭል በተባለ አስጎብኚ ድርጅት ውስጥ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ እንደመሆኗ፣ ድርጅቱ ሳይንስ የመሠከረላቸው የካርበን ልቀት የሚቀንሱ መንገዶች እንዲጠቀም ምክንያት ሆናለች።
የካርበን ልቀትን ከመቀነስ ጋር በተያያዘ መሥራት የሚፈልጉ አስጎብኚ ተቋማትን ለማስተማር መማሪያ መጽሐፍ በበይነ መረብ አዘጋጅታለች። ይህም 400 አስጎብኚ ድርጅቶች እና ባለሙያዎች በበጎ ፈቃዳቸው የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን ለመቀልበት የጀመሩት 'ቱሪዝም ዲክሌርስ' ንቅናቄ አካል ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ ላይ መሥራት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ተቋማት አሁን ላይ እተገነዘቡ መጥተዋል። የአካባቢ ጥበቃ ግብ በማስቀመጥ፣ ታዳሽ ኃይል ላይ ኢንቨስት በማድረግ፣ የካርበን ልቀትን መቀነስ የረዥም ጊዜ ግብ በማስቀመጥ እየተሰማሩ ነው።
ሱዛኔ ኤቲ
ሳራህ ኦት, አሜሪካ
መምህርት
በአሜሪካ ላይ ከተፈጸመው የ9/11 የሽብር ጥቃት ማግስት በፍሎሪዳ ግዛት የመካከለኛ ደረጃ መምህርት የሆነችው ሳራህ ለሐሰተኛ መረጃዎች ተጋላጭ ነበረች።
ምንም እንኳ ሳይንስ ብትማርም የአየር ንብረት ለውጥ እየተከሰተ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ነበራት።
ትክክል አለመሆኗን ማመኗ እውነትን ፍለጋ ለምታደርገው ጥረት የመጀመሪያ እርምጃዋ ነበር። የሕይወት ጉዞዋ የሳይንስ ትምህርት ብሔራዊ ማዕከል የአየር ንብረት ለውጥ አምባሳደር እንድትሆን አድርጓታል።
አሁን ላይ የፊዚክስ ሳይንስ ጽንሰ ሃሳቦችን ለማስተማር የአየር ንብረት ለውጥን ትጠቀማለች፣ እንዲሁም በምትኖርበት ማኅብረሰብ ውስጥ ስለ አካባቢ ጥበቃ የማንቃት ሥራ ትሠራለች።
ምንም እንኳ የአየር ንብረት ለውጥ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ጉዳይ ቢሆንም፤ ሁላችንም የተቻለንን ማድረግ አለብን። ማኅብረሰብ ማንቃት ጊዜን መመልከት ይጠይቃል። ጊዜውን ማክበር፤ ጊዜውን መምሰል አለብን።
ሳራህ ኦት
አራቲ ኩማር-ራኦ, ሕንድ
ፎቶ አንሺ
በደቡብ እስያ የምትሠራ ፎቶ አንሺ እና ፀሐፊ ናት። የናሽናል ጂኦግራፊክ አሳሽም ናት። አራቲ ኩማር-ራኦ የአየር ንብረት ለውጥ የፈጠረውን ለውጥ ትሰንዳለች።
የከርሰ ምድር ውሃ መቀነስ፣ የአካባቢ መውደም እና በኢንዱስትሪ መስፋፋት መሬት መነጠቅ ያለውን ተጽዕኖ በሥራዎቿ ታሳያለች። የብዝኃ ሕይወት መዛባት እና የጋራ መሬት እየቀነሰ መምጣቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍጥረታትን ለመጥፋት እየዳረጋቸው እንደሆነም ታሳያለች።
ለአሥርታት በሕንድ የሠራች ሲሆን፣ የአካባቢ ውድመት እንዴት ኑሮ እና ብዝኃ ሕይወትን እንደሚጎዳ በጽሑፎቿ አሳይታለች።
ማሪጅንላንድስ፡ ላንድስኬፕስ ኦን ዘ ብሪክ የተባለው መጽሐፏ በሕንድ አስቸጋሪ አካባቢዎች ያለውን ውጣ ውረድ ይዳስሳል።
የአየር ንብረት ለውጥ መነሻው ከመሬት፣ ከውሃ እና ከአየር ጋር ያለንን ትስስር ማጣታችን ነው። ትስስሩን መልሰን ማግኘት አለብን።
አራቲ ኩማር-ራኦ
ሶፊያ ኪያኒ, አሜሪካ
ተማሪ እና ማኅበራዊ ሥራ ፈጣሪ
በኢራን ካሉ ዘመዶቿ ጋር ከተነጋገረች በኋላ በቋንቋቸው ሶፊያ ኪያኒ ስለ አየር ንብረት ለውጥ በቂ ግንዛቤ እንደሌለ ተረዳች። ስለዚህም መረጃዎችን ወደ ፋርስ ቋንቋ መተርጎም ጀመረች።
ክላይሜት ካርዲናልስ የተባለ ፕሮጀክት ጀምራ ሥራዋ ሰፋ። ዓለም አቀፍ በወጣት የሚመራ ለትርፍ ያልተቋቋመ ፕሮጀክት ሲሆን፣ እንግሊዝኛ ለማይችሉ ሰዎች ስለ አየር ንብረት ለውጥ መረጃ በየቋንቋቸው ለማዳረስ ያለመ ነው።
በ80 አገራት 10 ሺህ ተማሪዎች ያሉት ሲሆን፣ በ100 ቋንቋዎች አንድ ሚሊዮን ቃላት ተርጉመዋል።
ሕልሟ የቋንቋ መሰናክልን አልፎ ሳይንሳዊ ዕውቀትን ማስፋፋት ነው።
ወጣት የመብት ተሟጋቾች የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት እና ነዳጅ መጠቀምን በመቃወም ትስስር ፈጥረዋል፣ ሚሊዮኖች ተቃውሞዎች አድርገዋል፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ፊርማዎች አሰባስበዋል፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብም አሰባስበዋል። የዓለም ችግሮች በርካታ ስለሆኑ በዕድሜ ወይም ተሞክሮ ተገድቦ መቆየት አያዋጣም።
ሶፊያ ኪያኒ
ቪ ካቲቩ, ዚምባብዌ/ዩኬ
ዩቲዩበር እና የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት አዘጋጅ
በማክዶናልድስ በትርፍ ጊዜዋ እየሠራች ነው የተማረችው። ከኦክስፎርድ እና ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲዎች ዲግሪ አላት። በትምህርት ያገኘችው ስኬት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በመላው ዓለም አነሳስቷል።
ዩኒቨርስቲ ሳለች የዩቲዩብ ገጽ ከፈተች። አነስተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ መማርን በተመለከተ ተሞክሮዋን ማካፈል ጀመረች። እንዴት ማጥናት እንደሚቻልም ትናገር ነበር።
ኢምፓወርድ ባይ ቪ' የተባለ ገጽ አላት። ከፍተኛ ትምህርት በመላው ዓለም ውክልና ላላገኙ ታዳጊዎች እንዲዳረስ ነው ንቅናቄ የምታደርገው።
ለወጣቶች ራስ-አገዝ መጽሐፍ የጻፈች ሲሆን፣ በትምህርት አስተዳደር የዶክትሬት ዲግሪዋን እየሠራች ነው።
ሁዳ ካታን, አሜሪካ
የመዋቢያ ምርቶች ንግድ መሥራች
ከኢራቅ ስደተኛ ቤተሰብ በአሜሪካ የተወለደችው ሁዳ ካታን ዕድገቷ አሜሪካ በኦክላሆማ ሲሆን፣ የልጅነት ሕልሟን ለማሳካት ዘልማዳዊን የቅጥር ሥራ አቋርጣለች።
በሎስ አንጀለስ ከተማ በሚገኘው እውቅ የውበት ማሠልጠኛ ትምህርቷን ከተከታተለች በኋላ ከዝነኛ ሰዎች እስከ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ንጉሥውያን ቤተሰቦች ደንበኛ ማፍራት ቻለች።
በኢንስታግራም ገጿ ከ50 ሚሊዮን በላይ ተከታዮችን ያላት ሲሆን፣ ከፍተኛ ተከታይ ያለው የውበት መጠበቂያ የንግድ ምልክት ባለቤት መሆን ችላለች።
ካታና እአአ 2013 ላይ ሁዳ ቢዩቲ የተሰኘ የውበት መጠበቂያ ምርቶቿን ይዛ ነው ወደ ገበያ የመጣችው። ዛሬ ላይ በቢሊዮን ዶላር የሚገመነው ኩባንያዋ፣ በመላው ዓለም ከ1500 በላይ በሚሆኑ መደብሮች ከ140 በላይ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን ለተጠቀሚ ያቀርባል።
ኦክሳና ዛቡዡኮ, ዩክሬን
ፀሐፊ
ከ20 በላይ ጽሑፎች አሏት። ከእነዚህም ውስጥ ልቦለድ፣ ግጥም፣ ኢ-ልቦለድ ይገኙበታል። ከዩክሬን ዋነኛ ደራሲዎች እና ምሁራን እንደ አንዷ ትታያች።
ፊልድ ወርክ ኢን ዩክሬኒያን ሴክስ' እና 'ዘ ሙዝየም ኦፍ አባንደንድ ሲክሬትስ' በተባሉ ሥራዎች ዓለም አቀፍ ዕውቅናን አግኝታለች።
ከኪዬቭ ሼቭቼንኮ ዩኒቨርስቲ በፍልስፍና የተመረቀች ሲሆን፣ በጥበባት ፍልስፍና የዶክትሬት ዲግሪ አላት።
መጽሐፎቿ በ20 ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። በሥራዎቿ በርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገራት ሽልማቶችን ለማግኘት ችላለች።
ሉሺያ ፌርትዝ, ጣልያን
ሞዴል እና ተጽዕኖ ፈጣሪ
ኢንስታግራም ላይ ከ235 ሺህ በላይ ተከታይ ያላቸው የ93 ዓመት ሰዎች ማግኘት ከባድ ነው። ሉሺያ ግን በጣልያን ስለ ሰዎች የአካል ገጽታ አውንታዊ ምልከታ እንዲኖር ንቅናቄ በማድረግ በዕድሜ ትልቋ ሰው ናቸው።
በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ኖረዋል። የ28 ዓመት ልጇን እና ባለቤቷን አጥተዋል።
የልጅ ልጃቸው የኢንስታግራም ገጽ ሲከፍትላቸው ግን ሕይወታቸው ተለወጠ። ደማቅ ቀለም ያለው ልብስ በመልበስ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ኮከብ ሆነዋል።
ግለ ታሪካቸውን የጻፉ ሲሆን፣ በ89 ዓመታቸው እርቃን የተነሱት ፎቷቸው ሮሊንግ ስቶን በተባለው ታዋቂ መጽሔት የፊት ገጽ ላይ ሞዴል ተደርጎ ቀርቧል።
ፌምኒስት እና የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች መብት ተሟጋች ናቸው። ስለ ሰውነት እና ዕድሜ ባለጸጎች በጎ ምልከታ እንዲኖር ጥረት እያደረጉ ነው።
ጃናቱል ፌርዱስ, ባንግላዲሽ
ከቃጠሎ የተረፈች
60 በመቶ የሰውነት ክፍሏን ከጎዳ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ተርፋለች። ፊልም ሠሪ፣ ፀሐፊ እና የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች ናት።
ቮይስ ኤንድ ቪውስ' የተባለ የሰብአዊ መብት ተቋም አላት። ከቃጠሎ የተረፉ ሴቶች መብት ላይ አተኩሮ ይሠራል።
አምስት አጫጭር ፊልሞች የሠራች ሲሆን፣ ሦስት ልብ ወለድ አሳትማለች። በታሪክ ነገራዋ አካል ጉዳተኞች የሚገጥማቸውን ታሳያለች።
በእንግሊዝኛ ሥነ ጽሑፍ ሁለተኛ ዲግሪ፣ በዴቨሎፕመንት ስተዲስ የመጀመሪያ ዲግሪ አላት።
ማቻ ፎርን-ኢን, ታይላንድ
የቀደምት ማኅበረሰቦች እና ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን መብት ተሟጋች
የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የግጭት ተጽዕኖ በሚታይበት የታይላንድ እና ሚያንማር ድንበር የምትኖረው ማቻ፣ የተገለሉ የማኅበረሰብ አካላት መብት ተሟጋች ናት።
ሳንጋሳን ያዋቾን ዴቨሎፕመንት የተባለ ፕሮጀክት መሥርታለች። መኖሪያ ወይም አገር የሌላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለማስተማር ነው የተቋቋመው። የቀደምት ማኅበረሰብ ሴቶች፣ ልጃገረዶች እና ወጣት የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ይገኙበታል።
አነስተኛ ከሆነ ቀደምት ጎሳ የተገኘችው ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዋ ፌምኒስት ማቻ፣ በቀጠናው ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት እንዲቆም ትሠራለች። የመሬት ባለቤትነት መብት እንዲከበር የአየር ንብረት ጥበቃ ፍትሕ እንዲሰፍን እንዲሁም የተገለሉ ማኅበረሰቦች መብት እንዲከበርም ትሠራለች።
ያለ ቀደምት ማኅበረሰቦች፣ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃያን፣ ሴቶች እና ልጃገረዶች ተሳትፎ ዘላቂነት ያለው የአካባቢ ጥበቃ ዕውን ሊሆን አይችልም።
ማቻ ፎርን-ኢን
ጄስ ፒፐር, ዩኬ
የአየር ንብረት ካፌ መሥራች
ክላይሜት ካፌ የሚባል ካፌ መሥርታለች። ማኅበረሰቡ ተገናኝቶ ስለአየር ንብረት ለውጥ የሚወያይበት ነው። ይህን በዓይነቱ የመጀመሪያ ካፌ ጄስ የከፈተችው በ2015 በስኮትላንድ በሚገኝ ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው።
ዓለም አቀፍ ትስስር ያላቸው ሌሎች እንደዚህ ዓይነት ቦታዎች እንዲፈጠሩ ድጋፍ ታደርጋለች።
ስለ አየር ንብረት ለውጥ ፍርሃታቸው እና ስጋታቸውን በነጻነት መነጋገር የሚችሉበት እንደሆነ ተጠቃሚዎች ይናገራሉ።
የሮያል ስኮቲሽ ጂኦግራፊካል ሶሳይቲ አባል እና የሮያል ሶሳይቲ ኦፍ አርትስ አባል ናት።
በአብዛኛው በሴቶች ቸ እና ልጆች የሚመራ የአየር ንብረት ለውጥ ንቅናቄ በየማኅበረሰቡ እየተፈጠረ ነው። ትስስሩ ለውጥን እያነሳሳ፣ ዕድሎችን እየጠረም መሆኑ ተስፋ ይሰጠኛል።
ጄስ ፒፐር
ሉዊዝ ማቡሎ, ፊሊፒንስ
አርሶ አደር እና ሥራ ፈጣሪ
በ2016 (እአአ) የተነሳው አውሎ ነፋስ በካማሪንስ፣ ሱር እና ፊሊፒንስ 80 በመቶ የእርሻ መሬት ላይ ጉዳት አድርሷል።
ሉዊዝ 'ዘ ካካዎ ፕሮጀክት' በሚል የጀመረችው ተቋም ይህን ችግር ተጋፍጧል። አገር በቀል የምግብ ሥርዓትን ዘላቂነት ባለው እርሻ እና ደን ጥበቃ ማዘመን ነው ዓላማው።
ሉዊዝ አርሶ አደሮችን በማብቃት አውዳሚ የምግብ ሥርዓት እንዲቆም ትሠራለች። አረንጓዴ ምጣኔ ሀብት እንዲስፋፋ ለማድረግ ኃላፊነቱን በአርሶ አደሮች ላይ በመጣል ነው ሥራዋን የምታከናውነው።
ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ አማካሪ ናት። በገጠር ያሉ ታሪኮችን እና ዕውቀትን ታስተጋባለች። የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ 'ያንግ ቻምፒየን ኦፍ ዘ ኧርዝ' ብሏታል።
እንደእኔ ባሉ የወደፊቱ ዓለም አረንጓዴ እንዲሆን በሚሹ እና ማኅበረሰብ በሚያስተሳስሩ ሰዎች ዓለም አቀፍ ንቅናቄ መካሄዱ ተስፋ ይሰጠኛል። ምግባችን ዘላቂነት ያለው፣ ምጣኔ ሀብታችንም ዑደት ያለው እንዲሆን እንዲሁም ፍትሕ እና እኩልነትን እንዲከተል እንሠራለን።
ሉዊዝ ማቡሎ
ካሮላይና ዲየዝ ፒሜንቴል, ፔሩ
ጋዜጠኛ
በ20ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ነው ኦቲዝም እንዳለባት የተነገራት። ይህንን ዜና ኬክ ጋግራ በበጎ ነበር የተቀበለችው።
አሁን በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ናት። ጋዜጠኛ ናት። ስለ አእምሮ ጤና ዘገባዎች ትሠራለች።
የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎች የሚግጥማቸውን መገለል ትታገላለች። የተለያዩ ፕሮጀክቶች እና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች አሏት። ከእነዚህም መካከል 'ማስ ኬ ባይፖላር' የሚባለውና 'ፔሩቪያን ኒውሮዳይቨርጀንት ኮሊዥን' ይጠቀሳሉ።
በፑልትዘር ሴንተር እና ሮዝሊን ካርተር በኩል የሚገኙ የጥናት ዕድሎች ተጠቃሚ ናት።
ጄትሱንማ ቴንዚን ፓልሞ, ሕንድ
የቡዲስት መነኩሴ
በ1940ዎቹ በእንግሊዝ ነው የተወለደችው። ወጣት ሳለች ነው ቡዲዝምን የተቀበለችው።
በ20 ዓመቷ ሕንድ ሄደች። በቲቤት የቡዲስት ገዳም በመቀባት የመጀመሪያዋ ምዕራባዊት ናት።
ሴቶች ያላቸውን ቦታ ከፍ ለማድረግ በፈጠረችው 'ዶንግዩ ጋትዊ ሊንግ ነነሪ' የተባለ የመነኩሴዎች ስብስብ ከ120 በላይ መነኮሳት ቤት እንዲያገኙ አስችሏል።
በሂማልያ ተራሮች ለ12 ዓመታት በጽኑ ተመስጦ በመኖር የበለጠ ትታወቃለች። በ2008 (እአአ) እምብዛም የማይሰጠው የክብር ማዕረግ 'ጄትሱንማ ' ተሰጥቷታል።
ላላ ፓስኩኔሊ, አርጀንቲና
አርቲስት
መጽሔት ሽፋን ላይ ያልወጡ ሴቶችን ማስተዋወቅ ነው ዋነኛው የላላ ግብ። በ2015 (እአአ) የመሠረተችው ድርጅት ውበት ምን ማለት ነው የሚለውን የሚያጠይቅ ነው። ውክልና በስፋት እንዲኖር እና ሴቶች በመገናኛ ብዙኃን ዕውቅና እንዲያገኙ ይሠራል።
ፕሮጀክቱ ስለ ሰውነት፣ እርጅና፣ አመጋገብ እና ተያያዥ ጉዳዮችን ያነሳል። #ሄርሜናሶላታፓንዛ የተሰኘ የማኅበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ አድርጋለች። ይህም ሴቶች በቦርጭ እንዳይሸማቀቁ ለማድረግ እና ሴቶች የተለያየ የሰውነት ክብደት ቢኖራቸውም ውበት እንዳላቸው ለማሳወቅ ነው።
ጠበቃ፣ ገጣሚ፣ ፌምኒስት እና የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዋ ላላ፤ ውበት ምን ማለት ነው የሚለውን በማኅበረሰቡ ለመለወጥ ትሠራለች። መደብን የሚለዩ፣ የፆታ መድልዎ ያላቸው እና ዘረኛ አካሄዶችን ለማስተካከል ትሠራለች።
መዝናኛ እና ስፖርት
ጂዮርጂያ ሃሪሰን, ዩኬ
የቴሌቪዥን አቅራቢ
ወሲባዊ ጥቃት ከደረሰባት በኋላ ታሪኳን ሴቶች ላይ የሚደርስ ወሲባዊ ጥቃትን ለመከላከል አውላለች። በዩናይትድ ኪንግደም ለማንኛውም ግንኙነት ፈቃደኛ መሆን ምን ማለት እንደሆነ የሚታይበትን መንገድ ለመለወጥ ሠርታለች።
ላቭ አይላንድ እና ዘ ኦንሊ ዌይ ኢዝ ኢሴክስ በተባሉ የቴሌቪዥን መሰናዶዎች ቀርባለች። በዩኬ ስለ በይነ መረብ ደኅንነት ማሻሻያ እንዲደረግ እና በቀድሞ የፍቅር አጋሮች 'ለበቀል' የሚለቀቅ ወሲባዊ ይዘት ያለው ምሥል ቁጥጥር እንዲሻሻል አስችላለች።
ሰዎች ያለ ፈቃዳቸው ምሥል ወይም ቪድዮ ሲለቀቅባቸው መክሰስ የሚችሉበት ጥብቅ የበይነ መረብ ሕግ እንዲኖር እየታገለች ነው።
ዲዮን ሊ, ደቡብ ኮርያ
የኬፖፕ4ፕላኔት መሥራች
ዲዮን ኬ ፖፕ በመጠቀም የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን ለመከላከል ትሞክራለች።
በ2021 ከመሠረተችው በኋላ በደቡብ ኮርያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ የመዝናኛ ዘርፍ ባለሙያዎችም እርምጃ እንዲወስዱ እና ወደ ታዳሽ ኃይል መዞር እንዲቻል ንቅናቄ ተደርጓል።
የአልበም ቅጂ ሲለቀቅ አካባቢ በመበከል የሚያሳድረውን ጫና በተመለከተ ግንዛቤ እንዲፈጠር ተደርጓል። የኬ ፖፕ ከዋክብት በበይነ መረብ ሙዚቃቸውን እንዲለቁም አስችሏል።
ዲዮን ከሙዚቃው ባሻገር ከኬ ፖፕ አቀንቃኞች ጋር የሚሠሩ ቅንጡ የፋሽን ተቋማትንም ለማሳተፍ እየሠራች ነው።
ለማኅበራዊ ፍትሕ ስንታገል ለውጥ ሳናመጣ አናቆምም። ይሄንንም ደጋግመን አሳይተናል። ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የምናደርገውን ትግል እንቀጥልበታለን።
ዲዮን ሊ
ጀስቲና ሚልስ, አሜሪካ
የምልክት ቋንቋ የመዝናኛ አቅራቢ
በየካቲት ወር በዓለም ከፍተኛ ተመልካች ባለው ሱፐር ቦል ላይ ጀስቲና ታሪክ ሠርታለች።
መስማት የተሳናት የመዝናኛ አቅራቢዋ ጀስቲና የሪሃናን ዘፈን ግጥም በምልክት ቋንቋ ለተመልካቾች በማሳየት ዝነኛ ሆናለች።
በሱፐር ቦል ጨዋታ እረፍት ላይ በአሜሪካ የምልክት ቋንቋ ሙዚቃ በማቅረብ ግንባር ቀደም ሆናለች። 'ሊፍት ኤቭሪ ቮይስ ኤንድ ሲንግ' የተባለውን ብሔራዊ መዝሙር በማቅረብም የመጀመሪያዋ ናት።
መስማት የተሳናቸው ውክልናቸውን ማሳየት ነው ግቧ። መስማት የተሳናቸው ነርሶች ለማሠልጠን የራሷን ተቋም መክፈትም ትመኛለች።
ዲያ ሚርዛ, ሕንድ
ተዋናይት
ተዋናይት ዲያ ሚርዛ በርካታ ሽልማቶች የተበረከቱላት በሕንድ ሲኒማዎች ላበረከተችው አስተዋጽ ብቻ ሳይሆን በአካባቢ ጥበቃ እና በሰብዓዊ ፕሮጀክቶች ላይ ባላት ተሳትፎ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም የበጎ ፈቃድ አምባሳደር እንደመሆኗ፤ ሚርዛ እንደ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ንጹሕ አየር እና የዱር እንስሳት ጥበቃ ባሉ ጉዳዮች ላይ መልዕክቶችን ታስተላልፋለች።
ሚርዛ "ሰዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያስችሉ ታሪኮችን ይሠራል" የምትለውን ኩባንያ 'ዋን ኢንዲ ስቶሪስ' የተባለ የታሪኮች ምስል እና ድምጽ ቀረጻ ኩባንያ አቋቁማለች።
የሴቭ ዘ ችልድረን እና ኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አኒማል ዌልፌር አምባሳደር ናት። የሳንክችዌሪ ኔቸር ፋውንዴሽን የቦርድ አባልም ናት።
አዚዛ ሳባይቲ, ሊባኖስ
የአጭር ርቀት ሯጭ
በሊባኖስ ፈጣኗ ሴት በሚል ነው የምትታወቀው። ይህም የሆነው የአገሪቱን 100 ሜትር ክብረ ወሰን ከሰበረች በኋላ ነው። በምሥራቅ እስያ እና አረብ ሻምፒዮና ላይ ለአገሯ ወርቅ በማስገኘት የመጀመሪያዋ ጥቁር አትሌት ናት።
ከላይቤሪያዊት እናት እና ከሊባኖሳዊ አባት የተወለደችው አዚዛ ወደ ሊባኖስ የሄደችው በ11 ዓመቷ ነው። ዘረኝነት እና ዘርን መሠረት ያደረገ መለየትን ተጋፍጣለች።
ራሷን ለማግኘት እና ለትልቅ ደረጃ ለማብቃት የጠቀማት አትሌቲክስ እና ለመብት መታገል ነው።
የደረሰችበትን ቦታ በመጠቀም ስለ ዘረኝነት በመናገር ለአካታችነት እና ለእኩልነት ትታገላለች። ከትምህርት ቤቶች እና ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበርም የሊባኖስ ወጣቶችን ለማነሳሳት ትሠራለች።
አንቲኒስካ ሴንቺ, ጣልያን
የፈረስ ላይ አክሮባቲስት
አንቲኒስካ ሴንቺ በ30ዎቹ ዕድሜ ነው በፈረስ ጀርባ ላይ አክሮባት የማሳየት ሙያ የጀመረችው። ከአሥር ዓመታት በኋላ ከጂምናስቲክ ቡድን ጋር ጉዞ እንደምታደርግ ግን አላሰበችም ነበር።
በሰሜን ጣልያን ላ ፊንስ ነው የተወለደችው። ሕይወቷ አልጋ በአልጋ አልነበረም። እናቷ የወሊድ ችግር ገጥሟቸው ስለነበር በሕይወት ትቆያለች ተብሎ አልታሰበም።
የጣልያን የቤተሰቦች እና የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ነው ወደ ሙያው እንድትገባ ምክንያት የሆናት።
የዓለም ሻምፒዮን ከሆነችው አና ካቫላሮ እና አሠልጣኝ ኔልሰን ቪዶኒ ጋር ሥልጠና እየወሰደች ትገኛለች።
አኒታ ቦንማቲ, ስፔን
እግር ኳስ ተጫዋች
ካታሎኒያ ግዛት ውስጥ ነው የተወለደችው። እግር ኳስ ተጫዋቿ አኒታ በስፔን ሊግ እና በቻምፒዮንስ ሊግ ለባርሴሎና በመጫወት ነው የምትታወቀው።
በዓለም ዋንጫ ወቅት በመላው ዓለም ታውቃለች። ስፔን ዋንጫውን እንድታነሳ ሦስት ግብ በማስቆጠር ከፍተኛ ሚና ነበራት። የጨዋታው ኮከብ ተብላለች። በ25 ዓመቷ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብላ ተመርጣለች።
በእግር ኳስ የሴቶች እኩልነት እንዲሰፍን ትታገላለች። በሜዳ ውስጥ እና ውጭም ለመብት በመሟገት ትታወቃለች።
አገሯ የዓለም ዋንጫ ስታገኝ ዜናው በስፔን እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ጄኒ ሄርሞሶ የተባለች የቡድኑን ተጫዋች ከንፈር መሳም ደብዝዞ ነበር። ሆኖም ግን የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብላ ስትሸለም ሴቶች የሚገጥማቸውን ተመሳሳይ ፈተና በንግግሯ ጠቅሳለች።
ዛንዲሌ ንዳሎቩ, ደቡብ አፍሪካ
የባሕር መጥለቅ አስተማሪ
የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት የባሕር መጥለቅ መምህርት ናት። ውቅያኖስ ተደራሽነት እንዲኖረው ትሠራለች።
ብላክ መርሜድ የተባለ ተቋም መሥርታለች። ወጣቶች እና ማኅበረሰቡን ከውቅያኖስ ጋር ያስተዋውቃል። ውቅያኖስን በመጠቀም ፈጠራ እንዲሁም ስፖርት እንዲስፋፋ ይሠራል።
ውቅያኖስን በማሰስ እና ፊልም በመሥራትም ዛንዲሌ ትታወቃለች። ክህሎቷን በመጠቀም ወጣቶች ስለ ውቅያኖስ እንዲያውቁ እና ስለ ባሕር ከፍታ መጨመር እንዲረዱ ታግዛለች። ይህም አካባቢን በተሻለ ለመጠበቅ ነው።
ስለ አየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ሳስብ ተስፋ የሚሰጠኝ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች መብዛታቸውን መገንዘቤ ነው።
ዛንዲሌ ንዳሎቩ
አሊስ ኦሴማን, ዩኬ
ፀሐፊ
ተሸላሚ ደራሲ፣ ሠዓሊ ናት። ለታዳጊዎች የጻፈችው ግራፊክ ልቦለድ ዝነኛ ነው። በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ታዳጊዎች ላይ ያተኮረው ጽሑፏ በኔትፍሊክስ የሚተላለፍ ተከታታይ ፊልም ሲሆን፣ የኤሚ ሽልማትን አግኝታለች።
በፊልሙ ጽሑፍ፣ ተዋንያን በመምረጥ እና በሙዚቃም ተሳትፋለች።
ለታዳጊዎች ሌሎችም መጻሕፍት ጽፋለች። 'ሬድዮ ሳይለንስ' እና 'ላቭለስ ኤንድ ሶሊቴር' የሚሉትን ያሳተመችው ገና በ19 ዓመቷ ነው።
መጽሐፍቶቿ ዋይኤ የመጽሐፍት ሽልማት፣ ኢንኪ ሽልማት፣ ካርኒጌ ሜዳል እና ጉድሪድስ ቾይስ አዋርድስ ጨምሮ ሌሎችንም ሽልማቶች ለማሸነፉ እና ዕጩ ለመሆን ችለዋል።
ሃርማንፕሬት ካውር, ሕንድ
ክሪኬት ተጫዋች
አምስት ምርጥ የክሪኬት ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ በመግባት ዘንድሮ የመጀመሪያዋ ሴት ሕንዳዊት ሆናለች።
የሕንድ ብሔራዊ የክሪኬት ቡድን አምበል ናት። በአገር ውስጥ እና በውጭ በተደረጉ ጨዋታዎች ኮከብ ናት። ቡድኗን በመምራት አምና ወደ ኮመንዌልዝ ጌምስ በማቅናት የብር ሜዳልያ ተሸላሚ ሆናለች።
በአገር ውስጥ ውድድር የሙምባይ ኢንዲያን ቡድን የሴቶች የክሪኬት ፕሪሚየር ሊግን እንዲያሸንፍ አስችላለች።
በ2017 የሙያዋ ከፍታ ነበር። በሴቶች ዓለም አቀፍ የክሪኬት ውድድር ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ከአውስትራሊያ ጋር በመጋጠም ለሕንድ ከፍተኛ የተባለ ነጥብ ያስገኘችበት ነበር። በዚህም ቡድኗ ወደ ፍጻሜው ጨዋታ እንዲያልፍ አስችላለች።
ቢያንካ ዊልያምስ, ዩኬ
አትሌት
የአውሮፓ እና የኮመንዌልዝ የ100 ሜትር ሩጫ አራት ጊዜ ወርቅ ሜዳልያ ያገኘች አትሌት ናት። በአውሮፓ ቻምፒዮና በ2023 ውድድር የታላቋ ብሪታኒያ እና ሰሜን አየርላንድ አምበል ነበረች።
ሐምሌ ላይ የ200 ሜትር የዩናይትድ ኪንግደም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሩጫ ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። በዚህም በቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒና ላይ ከእንግሊዝ ቡድን ጋር መጓዝ ችላለች።
በ2020 ከፍቅር አጋሯ አትሌት ሪካርዶ ዶስ ሳንቶስ ጋር ሲጓዙ በለንደን በፖሊስ እንዲፈተሹ ታዘዋል።
የፍቅር አጋሯ እና እሷም በይፋ ስለ ፖሊስ ፍተሻ እና ከጀርባው ስላው ዘረኛነት በይፋ ቅሬታ አቅርበዋል። ሁለት የፖሊስ አባላት ጥፋተኛ ሆነው ተገኝት ከሥራቸው ተባረዋል።
ኺኔ ህኒን ዋይ, ሚያንማር
ተዋናይት
በሚያንማር ትወና የጀመረችው ከ25 ዓመታት በፊት ነው። ሳን ዬ በተባለ ፊልም መሪ ተዋናይት ሆና ከተወነች በኋላ ታዋቂ ሆናለች። በሲኒማው በጣም ታዋቂ ናት።
አሁን የምትታወቀው በበጎ አድራጎት ሥራ ነው። በ2014 (እአአ) በስሟ ፋውንዴሽን መሥርታለች። ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናት እና የተጣሉ ልጆችን መንከባከብ ከሥራዎቹ መካከል ነው።
አሁን ወደ 100 ለሚደርሱ ልጆች እንክብካቤ ትሰጣለች። እነዚህ ልጆች ወላጆቻቸው በተለያየ ምክንያት ሊያሳድጓቸው ያልቻሉ ናቸው።
ሕገ ወጥ የልጆችን ዝውውር የመከላከል አምባሳደርም ናት።
አንድሬዛ ዴልጋዶ, ብራዚል
ኪውሬተር እና የባህል ማናጀር
ኮሚክ መጻሕፍት ትዕይንት በሳኦ ፖሎ በማዘጋጀት ነው የምትታወቀው። ይህንን መሰናዶ ፔሪፋኮን ብላዋለች።
ኮሚክ መጻሕፍት ደራሲዎች እና አርቲስቶች የሚገኙበት ነጻ መሰናዶ ነው። ባህላዊ ይዘት ያላቸው ሥራዎቻቸው እምብዛም ትኩረት ያላገኙ በተሻለ እንዲታወቁ ትሠራለች።
ኮሚክ መጻሕፍት፣ ቪድዮ ጌም እና ኮንሰር በማዘጋቸት ትታወቃለች። በ2023 (እአአ) 15 ሺህ ሰዎች መሰናዶው ላይ ተገኝተዋል።
ዩቲዩበር እና የፖድካስት አዘጋጅም ናት። በብራዚል ባህላዊ ሥራ ተደራሽነት እንዲሰፋ እና ጥቁር አርቲስቶች ዕውቅ እና እንዲያገኙ ንቅናቄ ታደርጋለች።
ዴሳክ ማዴ ሪታ ኩሱማ ዴዊ, ኢንዶኔዢያ
በፍጥነት ተራራ የመውጣት አትሌት
ዴስካ ማዴ ሪታ ኩስማ ዴዊ በባሊ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለች ግድግድ ላይ እንድትወጣ ከተጠየቀች በኋላ ነበር ከፍተኛ ነገሮች ላይ በፍጥነት መውጣት ፍቅድ ያደረባት።
ገና ልጅ ሳለች ነበር በወጣቶች ውድድር ላይ አሸናፊ መሆኑን የተለማመደችው፤ እአአ 2023 ላይ ግን ክብረ ወሰን በሆነው 6.49 ሰከንድ በአይኤፍኤስሲ የዓለም ከፍታ መውጣ ሻምፒዮንሺፕ ላይ አሸናፊ ስትሆን "ከፍታን በፍጥነት የምትወጣ የኢንዶኔዢያ ንግሥት" የሚል ስያሜን አስገኝቶላታል።
ይህ ድሏ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በሚካከተው ከፍታን በፍጥነት የመውጣት ውድድር ተሳታፊ እንድትሆን የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ሳታፊነቷን አረጋግጧል።
እስካሁን በኦሊምፒክ መድረክ በባድሜንተን፣ ክብደት ማንሳት እና ቀስት ውርወራ ሜዳሊያ ላገኘችው ኢንዶኔዢያ ሌላ አዲስ ታሪክን መጻፍ ትችል ይሆናል።
አን ግራል, ፈረንሳይ
ኮሜዲያን
ግሪንዋሺንግ የተባለ የኮሜዲ ክለብ አለ። የአካባቢ ጥበቃ፣ ፌምኒዝም፣ ድህነት፣ አካል ጉዳት እና የተመሳሳይ ፆታ አፍቃያን መብት የሚስተናገድበት ነው።
የመሠረተችው አን ግራል ናት። በቀልድ ሰዎችን የለውጥ አካል ማድረግ እና አእምሯቸውን እንዲሁም ልማዳቸውን መለወጥ እንደሚቻል ታምናለች።
ማኅበረሰቡ መዝናኛ ስለሚወድ አጫጭር መልዕክቶች ተቀባይነት ያገኛሉ። በማጋነን የሚፈጠር ቀልድ ስለ አየር ንብረት ለውጥ ለማሳወቅ አማራጭ እንደሆነ አን ትናገራለች።
ግሪንዋሺንግ ኮሜዲ ክለብ ስኬታማ መሆኑ ያስደስታል። ብዙዎች ስለ አየር ንብረት ለውጥ ግድ እንዳላቸው ያሳያል። መተባበር እንደሚፈልጉ፣ አብረው መሳቅ እና መታገል መቀጠል እንደሚፈልጉ ያሳያል!
አን ግራል
አሜሪካ ፌሬራ, አሜሪካ ፌሬራ
ተዋናይት
ተዋናይት፣ አዘጋጅ እና ፕሮዲውሰሯ አሜሪካ፣ ባርቢ፣ ሪል ዊሜን ሀቭ ከርቭስ እና አግሊ ቤቲ በተባሉት ፊልሞች ትታወቃለች። ሽልማቶችም ተበርክተውላታል።
አግሊ ቤቲ ተከታታይ የቴሌቭዥን ፊልም ላይ ከተወነች በኋላ ኤሚ በመሸለም በዕድሜ ትንሿ መሪ ተዋናይት ናት። የመጀመሪያዋ ላቲንም ናት። በስክሪን ላይ ውክልና እንዲኖር በማድረግ እና ለሴቶች መብት በመታገል ለዓመታት ትታወቃለች።
የተወለደችው ከሆንዱራ ስደተኛ ቤተሰብ ነው። በአሜሪካ የላቲኖችን ሕይወት የተሻለ ለማድረግ ለትርፍ ያልተቋቋመ 'ፖዴስታስ' የተባለ ድርጅት አቋቁማለች።
ካሚላ ፒሬሊ, ፓራጓይ
የኦሊምፒክ አትሌት
በ100 ሜትር ሩጫ ነው ካሚላ በቶኪዮ ኦሊምፒክስ ባለ ድል የሆነችው።
ጉራሪ ፓንተር በሚል ቅጽል ስም ትታወቃለች። የአገር አቀፍ ክብረ ወሰኖች ባለቤት ስትሆን የእንግሊዝኛ እና የስፖርት መምህርትም ናት።
በፓራጓይ ትንሽ ከተማ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት በሚሰጥ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደገችው። የአየር ንብረት ለውጥን በቅርበት መመልከት ችላለች።
የኢኮአትሌት ሻምፒዮን ናት። የስፖርት መድረኳን ተጠቅማ ስለ አየር ንብረት ለውጥ እና የካርበን ልቀት ቅነሳ ውይይት እንዲደረግ ታበረታታለች ማለት ነው።
የዱር እንስሳት በየቀኑ በሚታዩበት ከተማ ነው ያደግኩት። እነዚያ እንስሳት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየተሰቃዩ መሆኑን ማወቄ እንድረዳቸው ያነሳሳኛል።
ካሚላ ፒሬሊ
ፓራሚዳ, ጀርመን
ዲጄ እና የሙዚቃ ፕሮዲውሰር
አምና በኢራን ተቃውሞ ከመነሳቱ በፊት ዲጄ ፓራሚዳ በኢራን ተወላጅ ሴቶች ላይ ያለውን ባህላዊ ገደብ ስትታገል ነበር።
አሁን የምትሠራው በርሊን ነው። ወጣት ሳለች ቴህራን እና ፍራንክፈርት ስትኖር ነው ለሙዚቃ ያላትን ፍቅር ያወቀችው።
ላቭ ኦን ዘ ሮክስ' የተሰኘው አልበሟ መነሻው የዳንስ ሙዚቃ ታሪክ ሲሆን፣ የወቅቱ የዳንስ ባህል ላይ ያተኮረ ነው።
በበርሊን ፓኖራማ ባር ዲጄዋ ዓለም አቀፍ ተፈላጊ ዲጄ እና ስኬታማ የሙዚቃ ፕሮዲውሰር ሆናለች። በወንዶች የበላይነት ሥር ያለውን የሙዚቃ ዓለም በመታገል ትታወቃለች።
ፖለቲካ እና የማንቃት ሥራዎች
ሬኒታ ሆምስ, አሜሪካ
መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ተሟጋች
ሬኒታ ሆምስ ማያሚ ነው የምትኖረው። 'አወር ሆምስ' የተባለ ተቋም መሥራች ናት። ተቋሙ የንግድ እንዲሁም የማማከር አገልግሎት በፍሎሪዳ ይሰጣል።
የተገለሉ ማኅበረሰቦች የቤት ባለቤት የመሆን ዕድል እንዲያገኙ ንቅናቄ ታደርጋለች። የባሕር ውሃ መጠን ሲጨምር የተፈናቀሉ እንዲሁም የሚኖሩበት አካባቢ ቤት ዋጋ በመናሩ የተገፉ ማኅበረሰቦችንም ያካትታል።
አካል ጉዳተኛ ስትሆን፤ 11 ልጆች ባሏቸው እናት ነው ያደገችው።
በሴሎ ኢንስቲትዮት 'ኢምፓወሪንግ ሪዚሊያንት ዊሜን' በሚል ፕሮግራም ተካታለች። ሳይንስን መሠረት ባደረግ ትምህርት የአየር ንብረት ለውጥን ትታገላለች። ለአፍሪካውያን አሜሪካውያን እንዲሁም አቅመ ደካማ ሴቶች ቤት በሚሰጡ ተቋማትም ድጋፍ ታደርጋለች።
ከእናት መሬት ጋር ሴቶች ያለንን ቁርኝት ማወቅ ተስፋ ይሰጣል። ጠንካራ፣ ብርቱ፣ ለመንከባከብ የተፈጠርን፣ ተቆርቋሪ እና የድርጊት ሰዎች ነን።
ሬኒታ ሆምስ
ታማር ሙሴሪድዝ, ጆርጂያ
ጋዜጠኛ
በ18 ዓመቷ ነው የጆርጂያ መገናኛ ብዙኃን ላይ የቀረበችው። ታሙና በሚባል ስም የምትታወቀው ታማር ሙሴሪድዝ ሕይወቷ የተቀየረው በ31 ዓመቷ የማደጎ ልጅ እንደሆነች ስታውቅ ነው።
ወላጆቿን ለማግኘት ሁሉንም ነበር አቁማ ነው ፍለጋ የጀመረችው። ጥናት ስታደርግ በጆርጂያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ በጥቁር ገበያ ልጆች በማደጉ እንደሚሸጡ ደረሰችበት።
አይ አም ሰርቺንግ' የተባለ የፌስቡክ ገጽ ከፍታ በአብዛኛው ከሆስፒታል ስለሚሰረቁ ጨቅላ ሕጻናት እና ስለሕገ ወጥ ማደጎ አገር አቀፍ ውይይት እንዲደረግ መነሻ ሆናለች።
የከፈተችው ተቋም በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች እንዲገናኙ አስችሏል። እሷ ግን አሁንም ወላጆቿን እየፈለገች ነው።
ሞኒካ ማክዊልያምስ, ዩኬ
የቀድሞ ፖለቲከኛ እና የሰላም ተደራዳሪ
የሰሜን አየርላንድ 'ጉድ ፍራይዴይ' ስምምነት ከተፈረ 25 ዓመታት ተቆጥረዋል። ሞኒካ በዚህ ድርድር ቁልፍ ሚና ተጫውታለች። መድብለ ፓርቲ ላይ ያተኮረ የሰላም ንግግር ተደርጎ ስምምነት እንዲፈጠር ሠርታለች።
የሰሜን አየርላንድ የሴቶች ጥምረትን መሥርታለች። ይህም ክፍፍልን ወደ ጎን በመተው ሰላም ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ፓርቲ ነው።
በሰሜን አየርላንድ በሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር በመሆን ተመርጣለች። የሰሜን አየርላንድ መብቶችን ረቂቅ በማዘጋጀት ትታወቃለች።
ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን በመቃወም ጽሑፎች ያሳተመች ሲሆን፣ ታጣቂ ቡድንን በተመለከተ የሚሠራ ተቋም ኮሚሽነር ናት።
ዩላንዳ ምታባ, ማላዊ
የሕጻናት ጋብቻን ለማስቀረት የምትታገል
ዩላንዳ ምታባ ያደገችው ማላዊ ሊሎንግዌ ውስጥ በሚገኝ የተባለ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። ለሴቶች ትምህርት እምብዛም ድጋፍ የሚሰጥ አልነበረም። ሴቶች ትምህርት አቋርጠው 18 ዓመት ሳይሞላቸው ጋብቻ እንዲፈጽሙ ይገደዳሉ።
ዩላንዳ የማኅበረሰቡን አመለካከት በመስበር ከዩኒቨርስቲ መመረቅ ብቻ ሳይሆን ሁለተኛ ዲግሪም ሠርታለች።
ሴቶች ያለ ዕድሜ እንዳይዳሩ የሚከላከሉ ሕጎች እንዲተገበሩ ንቅናቄ ታደርጋለች። ዕድሜ ሳይደርስ ከማርገዝ ጋር የተያያዙ የጤና እክሎችን በተመለከተም ትሠራለች።
በአፍሪካ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ለሴቶች እኩል ተደራሽነት እንዲር በሚሠራው ኤጂኢ አፍሪካ የማላዊ ዳይሬክተር ሆና እየሠራች ነው።
ናጅላ ሞሐመድ-ላሚን, ምዕራብ ሰሃራ
የሴቶች መብት እና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች
ናጅላ የ'አልማስር ላይብረሪ ሴንተር' መሥራች ናት። በደቡብ ምሥራቅ አልጄሪያ በሚገኘው ሳሃራዊ የስደተኞች መጠለያ ሴቶች እና ሕጻናት ስለ ጤና እና አካባቢ ጥበቃ እንዲማሩ አድርጋለች።
ከ1975 (እአአ) ጀምሮ በሞሮኮ ይዞታ ሥር ባለው ምዕራብ ሰሃራ የተወለደች ሲሆን፣ ግጭትን በመሸሽ ቤተሰቧ ተሰዷል።
በስደተኞች መጠለያ ነው ያደረገችው። ወጣት ሳለች እንግሊዝኛ በመማር ለውጭ አገራት ልዑካን ታስተረጉም ነበር። ውጭ አገር ሄዳ ለመማርም ገንዘብ አሰባስባለች።
ዘላቂነት ባለው ዕድገት እና የሴቶች ጥናት ከተመረቀች በኋላ ወደ ስደተኞች መጠለያው ተመልሳለች። 200 ሺህ ሰሃራዊ ተፈናቃዮችን ለመርዳት በሚል ነው የተመለሰችው። በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየተባባሰ በመጣው በውሃ እና በምግብ እጥረት ተጽዕኖ ሥር ይገኛሉ።
በበረሃ የአየር ንብረት ለውጥ ያሳደረውን ጫና ልንገነዘብ ይገባል። ቤታችን በየጊዜው በጎርፍ እና በአሸዋ አውሎ ንፋስ እየተወሰደ ነው። ሕዝባችን በከፍተኛ ሙቀት እየተሰቃየ ነው። ለዚህ ሁሉ ቀውስ መባባስ ሕዝባችን ተጠያቂ አይደለም።
ናጅላ ሞሐመድ-ላሚን
ሴፒዴህ ራሽኑ, ኢራን
ፀሐፊ እና አርቲስት
አስገዳጅ ሂጃብ የመልበስ ሕግን በመቃወም ነው በኢራን ውስጥ ታዋቂ የሆነችው።
አውቶብስ ውስጥ ሂጃብ እንዲለበስ የሚያዘውን ሕግ ከምታስፈጽም ሴት ጋር ውዝግብ ውስጥ ከገባች በኋላ ለእስር ተዳርጋለች።
እስር ቤት እንዳለችም የበለዘ ፊቷ እየታየ በመንግሥት ቴሌቪዥን ላይ ቀርባ ለድርጊቷ 'ይቅርታ' ጠይቃለች። ይህ የሆነው በ2022 ሲሆን፣ ኢራን ውስጥ ከባድ ተቃውሞን ያስከተለው የማሳ አሚኒ በሥነ ምግባር ፖሊስ ከመገደሏ ከሳምንታት በፊት ነበር።
ከዚያም በኋላ ሴፒዴህ ራሹን ፀጉሯን ሳትሸፍን የተነሳቻቸውን ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በማጋራቷ ተከሳ ፍርድ ቤት ቀርባለች። በምታካሂደው ንቅናቄ ምክንያትም ከዩኒቨርስቲ እንደተባረረች ተናግራዋለች።
አሁን ከእስር ቤት ወጥታለች። ነገር ግን አስገዳጁን የሂጃብ ሕግ በመቃወም ቀጥላለች።
በርናዴት ስሚዝ, ተርትል አይላንድ/ካናዳ
የጠፉ ሰዎች ቤተሰቦች መብት ተሟጋች
በ2008 (እአአ) እህቷ ከጠፋች በኋላ መልስ ለማግኘት ያለመታከት ጥራለች።
በካናዳ ለጠፉ እና ለተገደሉ የቀደምት ማኅበተሰብ ሴቶች ቤተሰቦች ዋነኛ ተሟጋች ሆናለች። እርምጃ እንዲወሰድ እና ምላሽ እንዲያገኙ ጥምረት ፈጥራለች።
ድራግ ዘ ሬድ የተባለ ንቅናቄ አጋር መሥራች ናት። የጠፉ ሰዎችን አስክሬን እና ማስረጃዎችን በዊኒፒግ ሬድ ወንዝ አቅራቢያ የሚፈልግ ነው።
በማናቶባ ግዛት ምክር ቤት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ተመርጣለች። በቀጠናው በካቢኔ ሚኒስትርነት ከፈርስት ኔሽን ቀደምት ማኅበረሰብ በመመረጥ ሁለት ቀዳሚ ከሆኑ ሴቶች አንዷ ናት። የቤት፣ የሱስ እና ቤት አልባነት ጉዳይን የምትከታተል ሚኒስትር ናት።
ኢሪይና ስታቭቹክ, ዩክሬን
የአየር ንብረት ፖሊሲ አማካሪ
በአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲ የመሪነት ሚና አላት። ኢሪይና የአውሮፓ ኅብረት የአየር ንብረት ፋውንዴሽን ውስጥ የዩክሬን ፕሮግራም መሪ ናት። ዋነኛ ግቡ አረንጓዴ እና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ድኅረ ጦርነት መፍትሄ ለዩክሬን ማዘጋጀት ነው።
ከዚህ ቀደም ከ2019 እስከ 2022 በዩክሬን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ውስጥ በምክትል አስተዳደርነት ሠርታለች። በአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲዎች፣ አውሮፓን በማስተባበር፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በብዝኃ ሕይወት ዘርፍ ትታወቃለች።
ኢሪይና ሁለት የአካባቢ ጥበቃ ተራድኦ ድርጅቶች አጋር መሥራች ናት። ኢኮአክሽን እና ኪዬቭ ሳይክሊስትስ አሶሴሽን ይባላሉ። ቀጠናዊ የትስስር መድረኮች እንዲሁም የሲቪል ማኅበራት ሥራዎች በማስተባበር ትታወቃለች።
ባለንበት ቦታ እና ሁኔታ የተቻለንን ማድረግ አለብን። ሴንት ፍራንሲስ 'ተገቢ የሆነውን በማድረግ ጀምሩ እና የሚቻለውን ቀጥላችሁ ታደርጋላችሁ። ከዚያም የማይታሰበውን ስታደርጉ ራሳችሁን ታገኙታላችሁ' የሚለውን ጥቅሳቸውን አስታውሳለሁ።
ኢሪይና ስታቭቹክ
ግሎሪያ ስቴይኔም, አሜሪካ
ፌምኒስት መሪ
ከ1970ዎቹ አንስቶ የዓለም አቀፍ ፌምኒዝም ንቅናቄ መሪ ናት። ግሎሪያ ስቴይኔም በፌምኒዝም ያበረከተችው አስተዋጽኦ በመላው ዓለም ለዘመናት ዕውቅናን አስገኝቶላታል።
የመብት ተሟጋች፣ ጋዜጠኛ፣ ፀሐፊ፣ መምህርት እና የመገናኛ ብዙኃን ቃል አቀባይ በመሆን እኩልነትን ማስፈን ላይ ሠርታለች።
ሚስ' የተባለ መጽሔት ተባባሪ መሥራች ናት። መጀመሪያ መጽሔቷ የተሰራጨችው በ1971 ነበር። አሁንም እየታተመች ትገኛለች። መጽሔቷ የሴቶችን የመብት ንቅናቄ ወደ መገናኛ ብዙኃን በማምጣት ግንባር ቀደም ተደርጋ ትወሰዳለች።
ግሎሪያ ስቴይኔም በ89 ዓመቷ ፍትሐዊ ዓለም እንዲሰፍን መሥራት ቀጥላለች። ዊሜንስ ሚዲያ ሴንተር፣ ኢአርኤ ኮሊዥን እና ኢኳሊቲ ናው የተባሉ አንጋፋ ተቋማትን ትደግፋለች።
ያኤል በራውዶ-ባሃት, እስራኤል
ጠበቃ
የሕግ ባለሙያ የሆነችው በራውዶ-ባሃት ከ50ሺህ በላይ አባላት ያሉትን እና ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት የሚንቀሳቀሰው ዊሜን ዌጅ ፒስ ተባባሪ ዳይሬክተር ነች
ዊሜን ዌጅ ፒስ እአአ 2014 ላይ የተቋቋመ ሲሆን ሴቶች በሰላም ግንባት ሂደት ውስጥ በሚኖራቸው ተሳትፎ ላይ ትኩረት በማድረግ ነው። በዚህም የእስራኤል-ፍልስጤም ግጭት በፖለቲካዊ ድርድር መፍትሄ እንዲያገኝ ሲጥር ቆይቷል።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ዊሜን ዌጅ ፒስ የፍልስጤም የሴቶች እንቅስቃሴ ከሆነው ዊሜን ኦፍ ዘ ሰን ጋር ተባብሮ ሲሰራ ቆይቷል።
በራውዶ-ባሃት ባለውለታዬ የዊሜን ዌጅ ፒስ መሥራቾች መካከል አንዷ የነበረችው እና የሰላም ሰባኪዋ ቪቪያን ሲልቨር ነች ትላለች። ቪቪያን በእስራኤላውያን እና በፍልስጤማውያን መካከል እኩልነት እና መግባባትን ለመፍጠር ሕይወቷን የሰጠች ናት ትባለላች። ቪቪያን ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ በከፈተው ድንገተኛ ጥቃት ከተገደሉት መካከል አንዷ ነች።
ያስሚና ቤንስሊማኔ, ሞሮኮ
ፖለቲክስ4ኸር መሥራች
ለፆታ እኩልነት የምትታገለው ያስሚና፣ ወጣት ሴቶች እና ልጃገረዶች በፖለቲካ እና በውሳኔ ሰጪነት እንዲሳተፉ ታበረታታለች።
ባለፈው መስከረም ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ሞሮኮን ሲመታ፣ ከፆታ አንጻር ጥንቃቄ የተሞላበት እርዳታ የማቅረብ ሥራ እንዲከናወን ጥረት አድርጋለች።
በዚህም ሳቢያ አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ መገልገያ አቅርቦት ችግር እና የግዴታ ጋብቻን የመሳሰሉ ሴቶች እና ልጃገረዶች ሊገጥሟቸው የሚችሉትን ተግዳሮቶች አጽንኦት የሚሰጥ መግለጫ አውጥታለች።
በማማከር፣ በማሠልጠን እና የቦርድ አባል በመሆን በበርካታ ለትርፍ ባልተቋቋሙ ድርጅቶች አማካይነት ወጣት ሴቶች የመሪነት ክህሎት እንዲያዳብሩ ረድታለች። በሥራዋም የተባበሩት መንግሥታትን ሽልማትን አግኝታለች።
ሱሚያ ቶራ, አፍጋኒስታን
የስደተኞች መብት ተሟጋች
ዘ ዶስቲ ኔትዎርክ ለአፍጋኒስታናውያን ጠቃሚ መረጃ የሚሰጥ ተቋም ነው። አገልግሎቱ በአፍጋኒስታን እና በውጭ ላሉ ስደተኞችም ነው። ታሊባን አፍጋኒስታንን በ2021 ሲቆጣጠር ነው የተመሠረተው።
ሱሚያ አፍጋኒስታናዊ ስደተኛ ናት። ሰዎች ሲፈናቀሉ የሚገጥማቸውን ፈተና ኖራ አይታዋለች።
ስደተኞችን መልሶ በማቋቋም እና በግጭት ለተጎዱ ተማሪዎች ትምህርት በማዳረስ ትታወቃለች።
የትምህርትን ለውጥ የምትረዳው ሱሚያ ከተባበሩት መንግሥታት፣ ከዓለም ባንክ፣ ከማላላ ፈንድ እና ከሽሚት ፊውቸርስ ጋር በጋራ ሠርታለች። በአደጋ ውስጥ ያሉ ተፈናቃይ ሴቶች እና ልጃገረዶች ትምህርት እንዲያገኙ ነው የምትሠራው።
አሊሺያ ቻሁያ, ኢኳዶር
የቀደምት ማኅበረሰብ መብት ተሟጋች
የኢኳዶርን የአማዞን ደን ለማዳን በሚደረገው ትግል የምትሳተፈው አሊሺያ ዘንድሮ ድል ቀንቷታል።
ነሐሴ ላይ ኢኳዶራውያን በያሱኒ ብሔራዊ ፓርክ አዲስ የነዳጅ ቁፋሮ እንዳይደረግ ውሳኔ እንዲተላለፍ አስችለዋል። በብዝኃ ሕይወት በሚታወቀው አካባቢ ነዳጅ አውጪ ድርጅት ሥራውን እንዲያቆም ሆኗል። ይህ አካባቢ ባለው ብዝኃ ሕይወት ከዓለም ዕውቅ ሲሆን፣ ቀደምት ማኅበረሰቦችም ይኖሩበታል።
ያሱኒ ውስጥ የተወለደችው አሊሺያ በአካባቢው ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ለዓመታት ታግላለች።
የኢኳዶር የቀደምት ማኅበረሰብ ኮንፌደሬሽን ውስጥ የሴቶች ክንፍ መሪ ናት።
የአየር ንብረት ለውጥ ነገሮች እንዲከብዱብን አድርጓል። ሰብላችን በጎርፍ እየጠፋ ነው። ሙቀት ሲጨምር ድርቅ ይከሰታል። አብዛኛውን ምግባችንን እናጣለን። የተለፋበት ሰብል ሲጠፋ ደግሞ ያሳዝነናል።
አሊሺያ ቻሁያ
ኒማ ናማዳሙ, ዴሞክራቲክ ኮንጎ
የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች
ሂሮ ዊሜን ራይዚንግ በሚል የሴቶች እና ወጣቶችን ሕይወት የሚቀይር ንቅናቄ በኮንጎ ታካሂዳለች።
ኒማ ለአካል ጉዳተኞች መብት በመሟገት ሥራዋ ትምህርት እና ቴክኖሎጂን ትጠቀማለች። ይህም የሴቶችን ድምጽ ለማጉላት እና ለመብታቸው ለመታገል ነው።
በምሥራቅ ኮንጎ ገጠራማ አካባቢ ነው የተወለደችው። በሁለት ዓመቷ ፖሊዮ ይዟታል። ከጎሳዋ ከዩኒቨርስቲ ለመመረቅ የመጀመሪያዋ ሴት አካል ጉዳተኛ ናት።
የፓርላማ አባል ናት። በአገሪቱ የሥርዓተ ጾታ እና ቤተሰብ ሚኒስቴር አማካሪም ናት።
ማርያም አል-ኻዋጃ, ባህሬን/ዴንማርክ
የሰብአዊ መብት ተሟጋች
በባህሬን እና በባሕረ ሰላጤው አገራት ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲመጣ ነው ማርያም እንቅስቃሴ የምታደርገው።
የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥ ትታወቃለች። አባቷ አብዱላሂ አል-ኻዋጃ ከእስር እንዲፈቱ ባደረገችው ንቅናቄ ትታወቃለች። አባቷ ታዋቂ የመብት ተሟጋች ሲሆኑ፣ በባህሬን በ2011 (እአአ) ዴሞክራሲን የሚደግፍ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጋቸው የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።
ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ኮሚሽኖች ውስጥ ሠርታለች። የፌምኒስት ተቋም በሆነው ፍሪዳ እንዲሁም በፊዚሺያንስ ፎር ሂውማን ራይትስ ውስጥ ሠርታለች።
ሻምሳ አራዊሎ, ሶማሊያ/ዩኬ
ግርዛትን ለማስቀረት የምትሠራ
የሴቶችን ግርዛት ለማስቆም ነው ቆርጣ የተነሳችው። ትምህርት እና መረጃ በበይነ መረብ በመስጠት ትታወቃለች።
የተወለደችው ሶማሊያ ውስጥ ሲሆን የምትኖረው ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ነው። በስድሰት ዓመቷ ነው የተገረዘችው።
በቲክቶክ ላይ ከ70 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች ያገኘች ሲሆን፣ ማንም መረጃ ሳያገኝ መቅረት የለበትም በሚል ጥረት እያደረገች ነው።
በቤተሰቦቻቸው 'ለክብር' በሚል ጥቃት የሚደርስባቸውን ለመከላከል ትሠራለች። በተጨማሪም ለለንደን ፖሊስ ስለ ግርዛት አስከፊነት ምክር የምትሰጥ ሲሆን 'ጋርደን ኦፍ ፒስ' የተባለ የበጎ አድራጎት አቋቁማለች።
ሚሼል ኦባማ, አሜሪካ
ዐቃቤ ሕግ፣ ፀሐፊ እና ተሟጋች
የቀድሞ የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ በመላው ዓለም ሴቶች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የሚሠሩ ድርጅቶችን የሚደግፈው 'ገርልስ ኦፖርቹኒቲ አሊያንስ' መሥራች ነች።
ቀዳማዊት እመቤቷ ከባለቤታቸው ፕሬዝዳንት ኦባማ ጋር በመሆን በመላው ዓለም ያሉ ታዳጊ ሴቶች ጥራት ያለው የትምህር ዕድል እንዲያገኙ 'ሌት ገርልስ ለርን' የተሰኘ ንቅናቄ አስጀምረዋል።
ቀዳማዊት እመቤት ሆና ሌሎች ሦስት ንቅናቄዎችን አስጀምራለች፡ 'ሌትስ ሙቭ!' ወላጆች ጤናማ ልጆችን እንዲያሳድጉ የሚያስችል ንቅናቄ፤ የአሜሪካ መንግሥት ሠራተኞችን፣ ጡረተኛ የሠራዊት አባላትን እና ቤተሰቦቻቸውን የሚደግፍ 'ጆይኒንግ ፎርስስ' ንቅናቄ እንዲሁም ወጣቶች የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የሚያበረታታው 'ሪች ሃየር' ንቅናቄ።
ናታሳ ካንዲክ, ሰርቢያ
ጠበቃ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች
በ1990ዎቹ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ግጭት ከተነሳ በኋላ ናታሳ ካንዲክ በጦርነቱ የተፈጸሙ እንደ መድፈር፣ እንግልት፣ ግድያ፣ አስገድዶ መሰወር ያሉ ወንጀሎችን ሰንዳለች።
በቤልግሬድ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት የተለያየ ጎሳ ተወላጅ የሆኑ በርካታ ተጎጂዎችን ወክላ ተከራክራለች። በዚህም የሰርቢያ መንግሥት፣ ፖለቲከኛው ስሎቦዳን ሚሎቪክ ስለኮሶቮ ሕዝብ ያለውን ፖሊሲ መፈተሽ ተችሏል።
ሰብአዊ የሕግ ተቋም መሥርታለች። ያለ መድልዎ የጦር ወንጀል በመመርመር ይታወቃል።
አርኢሲኦኤም ሪኮንሳሊየሽን ኔትወርክ የተባለ ተቋም እንዲመሠረት ረድታለች። ይህም 130 ሺህ ሰዎች ስለሞቱበት ስለ ባልኪን ጦርነቶች እውነታዎች የሚሰበስብ ነው።
ሩክሻና ካፓሊ, ኔፓል
መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ተሟጋች
ኔዋ የተባለው የኔፓል ቀደምት ማኅበረሰብ ተወላጅ ናት። የትራንስጀንደር መብት ተሟጋችም ናት። ስለ ማንነት እምብዛም መረጃ በሌለበት ማኅበረሰብ ውስጥ ማድግ ለሩክሻና ቀላል አልነበረም።
ራሷን አስተምራ ስለ ፆታ እና ወሲባዊ ማንነት መገነዘብ ችላለች። ከታዳጊነቷ ጀምሮ ማንነቷን በይፋ በመግለጽ ስለ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች መብት መሟገት ቀጥላለች።
የሦስተኛ ዓመት የሕግ ተማሪ ናት። በኔፓል የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን የሕግ ምክር እንዲያገኙ በማስቻል ትታወቃለች።
በታሪክ ከተገለለ ማኅበረሰብ ነው የመጣችው። ሆኖም ግን የተገለለው የጁጊ ማኅበረሰብ ከቤት ንብረቱ እንዳይፈናቀል ንቅናቄ ታደርጋለች።
አማል ክሎኒ, አሜሪካ/ሌባኖስ
የሰብዓዊ መብቶች ጠበቃ
አማል ክሎኒ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ፍትሕን ለተነፈጉ መብት ስትሟጋት የቆየች እና ሽልማቶች የተበረከቱላት የሰብዓዊ መብቶች ጠበቃ ነች።
ከሥራዎቿ መካከል ዋነኞቹ በአርሜኒያ እና በዩክሬን በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ዙሪያ ከቀረቡ ክሶች ጋር በተያያዘ አስተዋጽኦ አድርጋለች። እንዲሁም በኬንያ እና በማላዊ በሴቶች ላይ የደረሱ ወሲባዊ ጥቃቶችን በተመለከተም የተለያዩ ሥራዎችን አከናውናለች።
በቅርቡ በአይኤስ ተዋጊዎች እና በዳርፉር የጦር አበጋዞች የተበደሉትን በመወከል ተከራክራ ስኬትን አስመዝግባለች። በአምባገነን መንግሥታት ጥርስ ውስጥ የገቡ ጋዜጠኞችን እና የፖለቲካ እስረኞችን ነጻ አውጥታለች።
በስመ ጥሩ የኮሎምቢያ ሕግ ትምህርት ቤት መምህርት ስትሆን፣ ከ40 አገራት በላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በደል ለደረሰባቸው ነጻ የሕግ አገልግሎት የሚሰጠው የ'ክሎኒ ፋውንዴሽን ፎር ጀስቲስ' መሥራቾች መካከል አንዷ ነች።
ሶፊያ ኮሳቼቫ, ሩሲያ
እሳት አደጋ ተከላካይ
የኦፔራ ዘፋኝ እና አስተማሪ የነበረችው ሶፊያ በ2010 (እአአ) ነው እሳት አደጋ ተከላካይ የሆነችው።
በጎ ፈቃደኞችን በማሠልጠን በሩሲያ ሰደድ እሳትን መከላከል እንዲቻል ሠርታለች። በመላው አገሪቱ ከ25 በላይ የበጎ ፈቃደኞች ቡድኖችን መሥርታለች።
በሩሲያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእሳት አደጋዎችን በማጥፋት ድጋፍ አድርጋለች። ግሪንፒስ ከተባለ ተራድኦ ድርጅት ጋር ትሠራ የነበረ ሲሆን፣ የሩሲያ መንግሥት ግን 'አላስፈላጊ ድርጅት' ብሎ ዘግቶታል።
በጎ ፈቃደኛ የእሳት አደጋ ተከላካዮችን ያሰባሰበ የበይነ መረብ ገጽ አላት። ሰደድ እሳትን በመቆጣጠር እና በመከታተል በሩሲያ ውጤታማ የተባለ ተቋም ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ ምንም ያህል የከፋ ቢሆን፣ ሁሉም ትልቅ ድል በትንንሽ ድሎች ይጀምራል። ትንሽ ነን በማለት በዓለም ደረጃ ለውጥ ማምጣት የማንችል ይመስለናል። ነገር ግን በአካባቢያችን ለውጥ በማምጣት መጀመር አለብን።
ሶፊያ ኮሳቼቫ
ዡ ዛውዛው, ቻይና
የሴቶች የዘር እንቁላልን አቀዝቅዞ የማቆየት መብት ተሟጋች
ሴቶች እርግዝናን ለማዘግየት እንቁላል እንዲያቆዩ በማድረግ የሚታወቀውን 'ኤግ ፍሪዚንግ' በ2018 ነው የሞከረችው። ሆኖም ግን እንቁላል ማቆየት የሚችሉት የተጋቡ ጥንዶች ብቻ እንደሆኑ በሕዝብ ሆስፒታል ተነገራት። እሷ አላገባችም ነበር።
ሆስፒታሉን ፍርድ ቤት አቁማለች። በቻይና ያላገቡ ሴቶች እንቁላል ማቆየት እንዲችሉ የሚሟገት በአገሪቱ የመጀመሪያው የፍርድ ቤት ጉዳይ ነበር።
በ2019 የተጀመረው የፍርድ ቤት ክርክር በቻይና ካለው አነስተኛ የወሊድ መጠን ጋር በተያያዘ መነጋገሪያ ሆኗል።
አሁንም ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አልሰጠም። ሆኖም ግን ዡ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ከወሰደች በኋላ ነገሩ የሕግ፣ ሕክምና እና ሥነ ምግባር ትምህርት ቤቶች ማስተማሪያ ሆኗል። ያላገቡ ሴቶች የወሊድ እና አካላዊ መብት ተሟጋች ናት።
ዴሄና ዳቪሰን, ዩኬ
የፓርላማ አባል
በ2019 ዴሄና የመጀመሪያዋ የወግ አጥባቂ የፓርላማ አባል ሆናለች። ይህም ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀ ከ1885 (እአአ) ወዲህ የመጀመሪያው ነው። በ2022 በማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ በማተኮር ሚኒስትር ሆናለች።
በ2023 እጅግ ስር የሰደደ ማይግሬን እንዳለባት በይፋ በማሳወቅ የሚኒስትርነት ሥራዋን ለቃለች።
በ13 ዓመቷ አባቷ በሰው እጅ ሲገደሉ ሕይወቷ ተለውጧል። በአባቷ ሞት ምክንያት በዩኬ ለፍትሕ የሚሠራ 'ፓርላሜንታሪ ግሩፕ ኦን ዋን ፓንች' የተባለ ፓርቲ መሥርታለች።
ስር የሰደደ ማይግሬን የተሻለ ሕክምና እንዲያገኝ ሠርታለች። የጡት ካንሰር ላይ የሚደረግ ምርምር ገንዘብ እንዲያገኝ ንቅናቄም አድርጋለች።
ሶኒያ ጉጃጃራ, ብራዚል
ሚኒስትር ዲኤታ
በብራዚል የሴቶች መብት ንቅናቄ ውስጥ ታዋቂ ናት። በ2023 ሶኒያ በብራዚል የመጀመሪያዋ የቀደምት ማኅበረሰብ ሚኒስትር ሆናለች። ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ይህንን ኃላፊነት መስጠታቸው መልካም ነው ተብሏል።
ዋነኛ ሥራዋ የአካባቢ ጥበቃን የሚገዳደሩ ወንጀሎችን መታገል እንደሆነ ተናግራለች።
አርቢዮዋ በተባለ አማዞን ውስጥ በሚገኝ አካባቢ ካልተማሩ ቤተሰቦች ነው የተወለደችው። የአየር ንብረት ለውጥ በብዝኃ ሕይወት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ማየት ችላለች።
ሥነ ጽሑፍ ካጠናች በኋላ ነርስ እና መምህርትም ሆና ሠርታለች። ከዚያ ወደ መብት ተሟጋችነት ገባች። በ2022 በሳኦ ፖሎ የመጀመሪያዋ የቀደምት ማኅበረሰብ ሴት የኮንግረስ አባል ሆናለች።
የአየር ንብረት ፍትሕ እንዴት ማስፈን እንደሚቻል እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዘ ዘረኝነትን እንዴት መዋጋት እንደሚቻል ማሰብ አለብን። አካባቢን በዋነኛነት መጠበቅ የሚችሉት ሰዎች ናቸው በአካባቢ ውድመት ጉዳት የሚደርስባቸው። ቀደምት ማኅበረሰቦች ብዝኃ ሕይወት በመጠበቅ ቀዳሚ ናቸው።
ሶኒያ ጉጃጃራ
ቤላ ጋሎስ, ምሥራቅ ቲሞር
የፖለቲካ አንቂ
ምሥራቅ ቲሞር ከኢንዶኔዥያ ነጻ ከመውጣቷ በፊት እና በኋላም ቤላ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ናት።
በስደት ሳለች ሕዝቡ ራሱን ማስተዳደር እንዲችል ንቅናቄ ስታደርግ ቆይታለች። ወደ አገሯ ከተመለሰች በኋላ በዓመታት ጦርነት ከደረሰው ውድመት ለማገገም በመልሶ መገንባት እና ግማሽ ሕዝቡን ከያዘው ድህነት ለማውጣት ሠርታለች።
በ2015 (እአአ) አረንጓዴ ትምህርት ቤት በመክፈት ዘላቂነት ያለው ዕድገት እንዲስፋፋ እና ልጆች የለውጥ አካል እንዲሆኑ ሠርታለች።
የምሥራቅ ቲሞር ፕሬዝዳንት አማካሪ ናት። በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን መብት እንዲሁም ሴቶችን በምጣኔ ሀብት በማብቃት ረገድ ታዋቂ ናት።
ሪና ጎኖይ, ጃፓን
የቀድሞ ወታደር
ሴት ወታደሮች ሪና የ11 ዓመት ልጅ ሳለች ከ2011 የመሬት መንቀጥቀጥ አድነዋታል። ከዚያ በኋላ ነው በጃፓን መከላከያ ውስጥ ለመሥራት ያሰበችው።
ወታደር ከሆነች በኋላ በየቀኑ ወሲባዊ ትንኮሳ ሲገጥማት የልጅነት ሕልሟ ጠለሸ።
መከላከያውን በ2022 ጥላ ወጣች። ሕዝባዊ ንቅናቄ ጀምራ በወንዶች የበላይነት በተያዘ ማኅበረሰብ ውስጥ ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ፍትሕ እንዲሰፍን ተጠያቂነት እንዲኖርም እየታገለች ነው። ወሲባዊ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች በይፋ ሲናገሩ ማኅበረሰቡ ዒላማ ያደርጋቸዋል።
በእሷ ንቅናቄ ምክንያት ጦር ሠራዊቱ ውስጥ ውስጣዊ ምርመራ ተደርጎ ከ100 በላይ የወሲባዊ ትንኮሳ ክሶች እንዲታዩ ተደርጓል። የመከላከያ ሚኒስቴርም ይቅርታ ጠይቋታል።
ክርስቲያና ፊጉሬዝ, ኮስታሪካ
ዲፕሎማት እና የአየር ንብረት ፖሊሲ ተደራዳሪ
በኮፐንሃገን በ2009 (እአአ) የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ውይይት ሲጀመር ክርስቲያና ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ነው የተገኘችው።
በተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ዋና ፀሐፊ በመሆን ለስድስት ዓመታት አገራት የተስማሙባቸውን የአየር ንብረት ለውጥ አሠራሮች እንዲጠብቁ ሠርታለች።
በእሷ ሥራ አማካይነት ወደ 200 የሚጠጉ ባለ ድርሻ አካላት የ2015 (እአአ) የፓሪስ ስምምነት ተፈራርመዋል። ይህ ስምምነት የዓለም ሙቀት ከኢንዱስትሪ መስፋፋት በፊት ወደ ነበረበት ተመልሶ ከ2.0 ሴሊሺየስ በታች እንዲሆን ነው።
ግሎባል ኦፕቲሚዝም የተባለ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሠራ ተቋም አጋር መሥራች ናት።
አንዳንዴ ስሜታዊ ስለምሆን መሥራት ይከብደኛል። አንዳንዴ ደግሞ እናደዳለሁ። ግን ደግሞ ይህንን ሐዘን እና ቁጣ ወደ ሥራ እለውጠዋለሁ። የተሻለ ዓለም በመፍጠር ለልጆቻችን ለማስተላለፍ እንደምንችል በማሰብ በትጋት እና በጥንካሬ፣ በፍቅር እና በተስፋ እሠራለሁ።
ክርስቲያና ፊጉሬዝ
ሳይንስ፣ ጤና እና ቴክኖሎጂ
አና ሃተነን, ፊንላንድ
የካርቦን ተጽዕኖ የቴክኖሎጂ ባለሙያ
ዘላቂነት ላይ አተኩራ የምትሠራው አና አረንጓዴ አካባቢን፣ ንጹህ አየርን በፊንላንዷ ላሂቲ ከተማ ታስተዋውቃለች። ከተማዋ የአውሮፓ አረንጓዴ ከተማ ተብላ በ2021 ተሸልማለች።
የከተማውን የካርበን ልቀት ቀንሶ ነዋሪዎች ገንዘብ እንዲያገኙ የሚያስችለው አሠራር መሪ ናት። በዓለም የመጀመሪያው የካርበን ንግድ መተግበሪያ ነው። ነዋሪዎች በሳይክል በመጓዝ ወይም የሕዝብ መጓጓዣ በመጠቀም ነው የካርበን ልቀትን የሚቀንሱት።
በኔትዚሮሲቲስ ውስጥ አማካሪ ስትሆን፣ ይህም የአውሮፓ ከተሞች የካርበን ልቀትን በ2030 እንዲገቱ የሚያስችል ነው።
ዘላቂነት ያለው አሠራርን ሌሎችም እንዲከተሉ ማድረግ ላይ ታተኩራለች። በሳይክል መንቀሳቀስ በከተማዎች ውስጥ እንዲዘወተር ትሠራለች።
በዓለም ዙሪያ ያሉ ማዘጋጃ ቤቶች ውስጥ ቀጣይነት ያለው አካሄድ ለዜጎች ለመስጠት የሚሠሩ ድንቅ ሰዎች አሉ። ሁላችሁም የለውጡ አካል ሁኑ!
አና ሃተነን
አስትሪድ ሊንደር, ስዊድን
የትራፊክ ደኅንነት መምህርት
ለዓመታት መኪና ሲሞከር የነበረው ግጭት ቢገጥም ምን እንደሚፈጠር በሚያሳዩ አሻንጉሊቶች ነበር። እነዚህ አሻንጉሊቶች ደግሞ በወንድ ተክለ ሰውነት አምሳያ የተሠሩ ናቸው። ሆኖም ግን በመኪና አደጋ የአካል ጉዳት ወይም ሞት ሊገጥማቸው የሚችለው በአምብዛኛው ሴቶች እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ።
አስትሪድ ኢንጂነር ናት። በዓለም የመጀመሪያውን በሴት ተክለ ሰውነት አምሳያ የተሠራ የመኪና መሞከሪያ አሻንጉሊት ሠርታለች። አሻንጉሊቶቹ የሴቶችን የሰውነት አቀማመጥ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው የተሠሩት።
የትራፊክ ደኅንነት መምህርት ናት። በስዊድን ብሔራዊ የመንገድ እና ትራንስፖርት ኢንስቲትዩት ውስጥ ነው የምትሠራው። በቻልመርስ ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርም ናት። የባዮሜካኒክስ እና የመንገድ አደጋ መከላከል ባለሙያ ናት።
ዋንጂራ ማታይ, ኬንያ
የአካባቢ ጥበቃ አማካሪ
በአህጉሪቱ ለሚገኙት ሁሉ አርዓያ መሆን የምትችለው ዋንጂራ ማታይ ለማኅበራዊ እና አካባቢ ጥበቃት የማንቃት ሥራ ስትሠራ ሁለት አስርት ዓመታት አልፈዋል።
ዋንጂራ በኬንያ አገር በቀል የሆነውን እና ዛፎችን በመትከል ሴቶችን ለማብቃት የሚሠራው 'ግሪን ቤልት ሙቭመንት' መሪ ናት። ይህ ንቅናቄ በ2004 (እአአ) የኖቤል የሰላም ተሸላሚ በነበሩት እናቷ ዋንጋሪ ማታይ የተጀመረ ነው።
ዎርልድ ሪሶርስስ ኢንስቲትዩት ውስጥ የአፍሪካ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ናት። የዋንጋሪ ማታይ ፋውንዴሽን ሊቀ መንበርም ናት።
በቤኖዝ ኧርዝ ፈንድ የአፍሪካ አማካሪ እንዲሁም በክሊን ኩኪንግ አሊያንስ እና በአውሮፓ ክላይሜት ፋውንዴሽን የአፍሪካ አማካሪ ናት።
ሁሉም በየማኅበረሰቡ ነው እርምጃ የሚወስደው። እጽዋት ላይ የተመሠረተ ንግድ፣ ታዳሽ ኃይል እና ማኅበረሰብ መር መልሶ ግንባታን ጨምሮ አገር በቀል ተነሳሽነቶችን መደገፍ አለብን። ምን ማድረግ እንደሚቻል ስለሚያሳዩኝ እነዚህ ጥረቶች ተስፋ ይሰጡኛል።
ዋንጂራ ማታይ
ኒሃ ማንካኒ, ፓኪስታን
አዋላጅ
ኒሃ ማንካኒ አምና ፓኪስታን በጎርፍ ስትጥለቀለቅ በየአካባቢው እየዞረች አገልግሎት ሰጥታለች።
ማማ ቤቢ ፈንድ የተባለ የተራድኦ ድርጅት አላት። በጎርፍ ለተጎዱ እና ከ15 ሺህ በላይ ለሆኑ ቤተሰቦች ነፍስ አድን የሆነ የማዋለጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ሰጥታለች።
አነስተኛ ገቢ ባላቸው ማኅበረሰቦች፣ በድንገተኛ አገልግሎት እና በአየር ንብረት ለውጥ የተጎዱ ማኅበረሰቦችን በመርዳት ላይ ታተኩራለች።
ማማ ቤቢ ፈንድ ባሰባሰበው ገንዘብ አምቡላንስ ገዝቶ ነፍሰ ጡር እናቶችን ከባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በአቅራቢያቸው ወዳሉ ሆስፒታሎች በመውሰድ አፋጣኝ ሕክምና እንዲያገኙ እተዘጋጀ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ባሳደረባቸው አካባቢዎች የአዋላጆች ሚና ከፍተኛ ነው። መጀመሪያ ደርሰን ድጋፍ የምሰጠው እኛ ነን። የአካባቢ ተቆርቋሪም ነን። ሁኔታዎች ቢባሳሱ እንኳን ሴቶች የእርግዝና፣ የወሊድ እንዲሁም ድኅረ ወሊድ አገልግሎት እንዲያገኙ እንሠራለን።
ኒሃ ማንካኒ
ኢሳቤል ፋሪያስ ሜየር, ቺሊ
ቀድሞ የማረጥ አንቂ
ኢሳቤል የወር አበባዋ ሲዛባ ከባድ ችግር ይሆናል ብላ አልገመተችም። ግን በ18 ዓመቷ ቀድሞ ማረጥ እንደገጠማት አወቀች። ይህም ከ40 ዓመት በታች ካሉ ሴቶች ውስጥ 1 በመቶ በሚሆኑት ላይ ብቻ የሚከሰት ነው።
በዚህም ምክንያት የማረጥ ምልክት ሴቶች ማሳየት የሚጀምሩት በጣም ቀድሞ በወጣትነት ዕድሜያቸው ሲሆን፣ ኢሳቤል ይህ እንዴት ሕይወቷ ላይ ጫና እንዳሳደረ በግልጽ ትናገራለች።
የ30 ዓመቷ ጋዜጠኛ በላቲን አሜሪካ ቀድሞ ማረጥ የገጠማቸው ሴቶች የትስስር መድረክ ፈጥራለች። መረጃ በመለዋጥ የሚደጋገፉበት ነው።
ሩማይታ አል ቡሳይዲ, ኦማን
ሳይንቲስት
በ2021 ያቀረበችው የቴድ ቶክ ንግግር ርዕስ ሴቶች እና ልጃገረዶች ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ማምጣት እንደሚችሉ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ይህንን ንግግር ተመልክተዋል። የአረብ የሴቶች መብት ቁንጮም ተብላለች።
በኦማን በወጣቶች የአየር ንብረት ለውጥ እና አካባቢ ጥበቃ ኮሚቴ ውስጥ ቁልፍ ቦታ አላት።
የአየር ንብረት ለውጥን ያማከለ የውጭ እርዳታ በማድረግ ረገድ የባይደንን አስተዳደር አማክራለች። የግሪንላንድ መንግሥትን ዘላቂነት ባለው ቱሪዝም ዙሪያ አማክራለች።
ደቡብ ዋልታ በመድረስም በዕድሜ ትንሿ የኦማን ሴት ናት። ዊሜኤክስ የተባለ እና አረብ ሴቶች የንግድ ድርድር ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ የሚረዳ ተቋም አላት።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አንደኛው መፍትሄ ሴቶች እና ልጃገረዶችን ማብቃት ነው። በማኅበረሰባቸው ውስጥ የሚኖራቸው ሚና ቤታችን የሆነችው ምድርን እንድንጠብቃት ይረዳል።
ሩማይታ አል ቡሳይዲ
ኦሌና ሮዝቫዶቭስካ, ዩክሬን
የልጆች መብት ተሟጋች
የዩክሬን ሕጻናት ጦርነቱ ያሳደረባቸውን ተጽዕኖ እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ በማሰብ ነው የምትሠራው። 'ቮይስስ ኦፍ ችልድረን' በሚል ለትርፍ ያልተቋቋመ የሥነ ልቦና ድጋፍ መስጫ መሥርታለች።
በ2019 ነው ድርጅቱ ሥራውን የጀመረው። በዶንባስ በሩሲያ የሚደገፉ ኃይሎች ከዩክሬን ጋር መዋጋት ሲጀምሩ በውጊያው አካባቢ ለመሥራ ሄዳለች።
ተቋሙ 100 የሥነ ልቦና ባለሙያዎች፣ 14 ማዕከሎች እና ነጻ የእርዳታ ጥሪ መስመር አለው። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሕጸናት እና ወላጆችን ረድቷል።
ለኦስካር በታጨው 'ሐውስ ሜድ ኦፍ ስፕሊንተርስ' ዘጋቢ ፊልም ተሳትፋለች። 'ዋር ስሩ ዘ ቮይስስ ኦፍ ችልድረን' የሚል መጽሐፍም አሳትማለች።
ሱሚኒ, ኢንዶኔዥያ
የደን ጥበቃ ባለሙያ
በኢንዶኔዥያ አቼ ግዛት ጥብቅ ደን ውስጥ ሴቶችን አመራር ቦታ ላይ ማየት የተለመደ አይደለም።
ሱሚኒ በመንደሯ ዋነኛ የጎርፍ መንስኤ እና ለአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የደን መጨፍጨፍ እንደሆነ ስታውቅ እርምጃ ለመውሰድ እና ከሌሎች የማኅበረሰቡ ሴቶች ጋር ለመሥራት ወሰነች።
የዳማናን ባሩ መንደር ነዋሪዎች 251 ሄክታር የሆነውን አካባቢ ለ35 ዓመታት ለመጠበቅ ከአካባቢ እና ደን ጥበቃ ሚኒስቴር ፈቃድ አግኝተዋል።
በመንደሩ የደን ጥበቃ ክፍልን ሱሚኒ ትመራለች። የአካባቢውን ነብሮች እና ሌሎችም እንስሳት አደጋ ውስጥ የጣለው አደን እንዲቆም ትሠራለች።
በደን ጭፍጨፋ እና አደን ሳቢያ ደኖች የበለጠ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ነው። የአየር ንብረት ለውጥን እንዴት በጋራ እንከላከላለን በሚለውና ነፍሳትን በመጠበቅ ረገድ የበለጠ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
ሱሚኒ
ናታሊ ሳይላ, ማልታ
የሕክምና ዶክተር
በማልታ ጽንስ ማቋረጥን የተመለከቱ ሕጎች ጥብቅ ናቸው። ሴቶች ምክር እና መረጃ እንዲያገኙ ሐኪሟ ትረዳለች።
ዶክተርስ ፎር ቾይስ በሚል ጽንስ ማቋረጥ ከወንጀል ድርጊትነት እንዲወጣ፣ ጽንስ ማቋረጥን በሚመለከት ሕግ ዙሪያ እና በእርግዝና መቆጣጠሪያ ተደራሽነትን ዙሪያ የሚሠራ ተቋም አጋር መሠራች ናት።
ሴቶች ሕይወታቸው በእርግዝና አደጋ ውስጥ ከወደቀ ብቻ ማስወረድ በሚፈቀድባት ማልታ በርካቶች መድኃኒት በመውሰድ ያለ ተገቢ የሕክምና ድጋፍ ጽንስ ለማቋረጥ ይገደዳሉ። ሴቶችን ከውርጃ በፊት እና በኋላም የሚደግፍ ተቋም አላት።
ስለ ወሲብ መረጃ የሚሰጡ መጻሕፍት የጻፈች ሲሆን፣ በ10 እና 13 ዓመት ዕድሜ ላሉ ዕውቀት ለማስጨበጥ ያለመ ነው። ስለ ሥነ ተዋልዶ ጤና መረጃ እንዲኖር ትሠራለች።
ባያንግ, ቻይና
የቀን ውሎ ፀሐፊ እና አማካሪ
ባያንግ ከ2018 ጀምሮ ከባቢ አየርን በተመለከት የቀን ውሎ ትጽፋለች። እነዚህም አገር በቀል ችግኞችን በመንከባከብ የውሃ አካልን በመጠበቅ እና የአየር ሁኔታን በመመዝገብ ላይ ያተኮሩ ናቸው።
በቻይና ኩጋሂ ግዛት ነው የምትኖረው። ስፍራውም በቲቤት ተራራ አካባቢ ነው የሚገኘው። የሙቀት መጨመር፣ የበረዶ ግግር መቅለጥ እና የደን ውድመትን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥ እየጎዳው የሚገኝ አካባቢ ነው።
ባያንግ የ'ሳንጂይናግዩም ዉሜን ኢንቫይሮምንታሊስትስ ኔትወርክ' አባል ናት። ይህም በማኅበረሱ ውስጥ ጤና እና ዘላቂነትን አስመልክቶ ይሠራል።
ለአካባቢ ተስማሚ ምርቶች ታዘጋጃለች። እነዚህም የከንፈር ቅባት፣ ሳሙና እና ቦርሳን ያካትታሉ። ይህም ውሃን ለመንከባከብ እና ብዙኃኑን በአካባቢ ጥበቃ ለማነሳሳት ነው።
አናማሪያ ፎንት ቪላሮኤል, ቬኔዝዌላ
የፊዚክስ ሳይንቲስት
የፓርቲክል ፊዚክስ ተመራማሪ ናት። ፓርቲክሎች (ቅንጣቶች) ለመረዳት እና በጥቃቅን ሞዴሎች ለማስቀመጥ ትሠራለች።
ሥራዎቿ ዘርፉን የበለጠ ለመረዳት አግዘዋል። ብላክ ሆልን እና ኳንተም ግራቪቲን ለመረዳት እንዲሁም የመጀመሪያውን የቢግ ባንግ ክስተትን ለመረዳት የሚረዱ ሥራዎች አሏት።
የፋውንዴሲዮን ፖላር ተሸላሚ ናት። በዩኒስኮ ሳይንስ ውስጥ ባሉ ሴቶች ዝርዝር ከቬኔዝዌላ የዘንድሮ ተሸላሚ ናት።
ፋቢዮላ ትሬጆ, ሜክሲኮ
ማኅበረሰባዊ የሥነ ልቦና ባለሙያ
ሙያዊ ጉዞዋን ከሁለት አሥርታት በፊት ስትጀምር በሜክሲኮ የሴቶች ወሲባዊ እርካታ እና ማኅበራዊ ፍትሕ ላይ ያተኮረ ጥናት እምብዛም አልነበረም።
ፋቢዮላ በሥራዎቿ ማኅበራዊ እኩልነት ማጣት፣ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ላይ በማተኮር ለሴቶች ወሲባዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ትታገላለች።
እኩልነት ማጣት ሴቶችን ለወሲባዊ ብዝበዛ ተጋላጭ እንደሚያደርግ ትናገራለች። ንግግሮች በማድረግ፣ ጥናት በመሥራት፣ በወርክሾፖች አማካይነትም ስለ ወሲባዊ እርካታ ሰዎችን ለማስተማር ትሠራለች።
ለላቲን አሜሪካ እና ስፓኒሽ ቋንቋ ለሚናገር ማኅበረሰብ በሚሆን መንገድ ነው የምትሠራው። በእነዚህ ማኅበረሰቦች ስለ ሴቶች ጤናም ይሁን ስለወሲብ ማውራት እንደ ነውር ይቆጠራል።
ሱዛን ቾምባ, ኬንያ
ሳይንቲስት
የዎርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ናት። በልጅነቷ በማዕከላዊ ኪሪያጋ ግዛት በድህነት መኖሯ መነሻ እንደሆናት ትናገራለች። ልጅነቷ የሰዎችን ሕይወት መለወጥ እንድትሞክር መነሻ ሆኗታል።
ደኖችን በመጠበቅ፣ መሬት እንዲያገግም በማድረግ እና የአፍሪካን የምግብ ሥርዓት በማደስ ላይ ነው ሥራዋ የሚያተኩረው።
በኮንጎ ደን ውስጥ፣ በረሃማው የምዕራብ አፍሪካ ሳህል እና በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም ከሴቶች እና ከወጣቶች እንዲሁም ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ጋር ትሠራለች። መሬታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ ነው የምትታወቀው።
ከመንግሥት እና ከአጥኚዎች ጋር ግኝቶቿን በመጋራት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ጠንካራ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ትጥራለች።
በተለይም ዋና የካርበን ልቀት ያለባቸው አገራት እና በምጣኔ ሀብት ያደጉ መሪዎች እርምጃ አለመውሰዳቸው ይጎዳኛል። እርምጃ የማይወስዱት በገንዘብ፣ በኃይል እና በፖለቲካ ምክንያት ነው። ይሄንን ስሜት የምቋቋመው በመላው አፍሪካ ካሉ ሴቶች እና ወጣቶች ጋር በመሥራት ነው። ሥራችን ተፈጥሮን ለመጠበቅ እና ለማገገም እንዲሁም የምግብ ሥርዓትን ለማሻሽና ፖሊሲን ለማጠየቅ ነው።
ሱዛን ቾምባ
ሳራ አል-ሳቃ, የፍልስጤም ግዛቶች
አጠቃላይ የቀዶ ጥገና ሐኪም
ዶ/ር ሳራ አል-ሳቃ በጋዛ ውስጥ የመጀመሪያዋ እውቅና ያላት ሴት የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ስትሆን፣ የምትሠራውም በትልቁ የአል-ሺፋ ሆስፒታል ውስጥ ነው።
ሳራ አል-ሳቃ በጋዛው ጦርነት ውስጥ እየተካሄደ ለሰዎች የምትሰጠውን ሕክምናን በተመለከተ በኢንስታግራም ገጿ ላይ መረጃዎችን ታሰባስባለች። እስራኤል በሐማስ ላይ የምታካሂደውን ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት ጊዜ አል-ሺፋ ሆስፒታል ከባድ ጉዳት ደርሶበታል።
ሳራ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጿ ላይ ሆስፒታሉ ህሙማንን በአግባቡ ለማከም እንቅፋት ስለሆኑበት የኤሌክትሪክ መቋረጥ፣ የነዳጅ፣ የውሃ እና የምግብ እጥረትን በተመለከተ መረጃዎችን ስታጋራ ቆይታለች። የእስራኤል ወታደሮች ሐማስን ኢላማ በማድረግ በሆስፒታሉ ላይ ወረራ ከመፈጸማቸው ቀደም ብላም አል-ሺፋን ለቃ ወጥታለች።
ሳራ ተወልዳ ያደገችው ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2010 ነበር ወደ ጋዛ የሄደችው። ጋዛ ውስጥ በሚገኘው ኢስላሚክ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ሕክምናን አጥንታለች። እንዲሁም በለንደኑ ኪዊን ማሪ ዩኒቨርስቲ ደግሞ ቀዶ ሕክምናን ተምራለች። የእሷን ፈለግ በመከተልም በርካታ ሴት የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች በመሆናቸው ጋዛ ውስጥ ብቸኛዋ ሴት የቀዶ ሕክምና ባለሙያ መባሏ አብቅቷል።
አሚና አል-ቢሽ, ሶሪያ
በጎ ፈቃደኛ ነፍስ አድን ሠራተኛ
የሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት በ2017 (እአአ) ሲፋፋም አሚና ከመጀመሪያዎቹ በጎ ፈቃደኛ የሶሪያ ሲቪል መከላከያ አባል መካከል አንዷ ነበረች። ለተጎዱ ሰዎች ድጋፍ ለመስጠት እና የመጀመሪያ እርዳታ ለመስጠት ነበር የሚንቀሳቀሱት።
ኋላ ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ ጉዳት ያደረሰባቸው ሰዎችን በሶሪያ እና ቱርክ በ2023 ለመርዳታ በጎ ፈቃደኛ ሆናለች። ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ ቤተሰቦችን ያሸበረ እና ከፍርስራሽ ሥር ያስቀረ ነው።
አሁን በሰሜን ሶሪያ የሌሎች ሴቶችን ሕይወት የተሻለ ለማድረግ እየሠራች ነው። በቢዝነስ አድምንስትሬሽን የዲግሪ ትምህርቷን እየተከታተለች ነው። ሕልሟ በሶሪያ ውስጥ ሰላም ለማስፈን የበኩሏን ማበርከት ነው።
ባሲማ አብዱራህማን, ኢራቅ
የአረንጓዴ ግንባታ ነጋዴ
በ2014 (እአአ) ኢስላሚክ ስቴት የተባለው ቡድን በኢራቅ የተወሰኑ ቦታዎችን ሲይዝ ባሲማ በአሜሪካ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበረች።
በግጭቱ ብዙ ከተሞች ወድመዋል። ባሲማ በስትራክቸራል ኢንጂነሪንግ ሁለተኛ ዲግሪ ይዛ ወደ አገሯ ስትመለስ እንዴት መርዳት እንደምትችል አስተዋለች።
በኢራቅ የመጀመሪያውን አረንጓዴ (ተፈጥሮ የማይጎዳ) ግንባታ ኬኢኤስኤን መሠረተች። አዳዲስ ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች እና የኢራቅን ባህላዊ ግንባታ በማዋሃድ አረንጓዴ ግንባታ እንደሚቻል አሳይታለች።
የዛሬ ሕንጻዎች ለወደፊት ደኅንነት አስጊ እንዳይሆኑ ትሠራለች።
ስለ አየር ንብረት ለውጥ አብዝቼ እጨነቃለሁ። ለዚህ ችግር መፍትሄ መሆን ሳይችል የቀረ ሰው እንዴት በሰላም እንደሚኖር ይገርመኛል።
ባሲማ አብዱራህማን
ጄኒፈር ኡቼንዱ, ናይጄሪያ
የአእምሮ ጤና አንቂ
በጄኒፈር ኡቼንዱ የተመሠረተው በወጣት የሚመራው ባለ ራዕይ ድርጅት የሆነው ሰስቲቫይብስ፤ ዘላቂ ነገሮችን ተግባራዊ እና ምቹ እንዲሆኑ ይጥራል።
የኡቼንዱ የቅርብ ጊዜ ሥራዎች ትኩረት ያደረጉት ወጣት አፍሪካውያን በአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ምክንያት የሚደርስባቸው ቀውስ ላይ ነው።
እአአ በ2022 በጥናት የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካውያን የአእምሮ ጤና እና ሕክምና ላይ የሚደርሰውን ጫና የሚመረምር ዘ ኢኮ-አንዛይቲ አፍሪካ ፕሮጀክት አቋቁማለች።
ዓላማዋ የአየር ንብረት ለውጥ በአእምሮ ጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ከሚሠሩ ግለሰቦች እና ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት ነው።
የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የተለያዩ ስሜቶች ይሰሙኛል። ምንም እንኳ ሁሉንም ነገር ማድረግ ባልችልም በተቻለኝ አቅም የራሴን አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሌን ሳስብ የአእምሮ ሰላም ይሰጠኛል። ከሌሎች ጋር በመተባበር መሥራት በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጡ ስሜቶችን ለመጠበቅ ያሰችለኛል።
ጄኒፈር ኡቼንዱ
ሊያን ከሊን-አንስወርዝ, ዩኬ
የውሃ አካላት ሳይንቲስት
የውሃ አካላት ለመኖሪያነት አስቸጋሪ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ካርበንን በማከማቸት ለዓሳ መራቢያነት በማዘጋጀት ትታወቃለች።
ሊያን ፕሮጀክት ሲግራስ የተባለ ተቋም መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ናት። በዩኬ ግንባር ቀደሙ የዘርፉ ተቋም ነው።
በሮቦት የሚሠራ መቆጣጠሪያን በመጠቀም ዘር ለመትከል የሚያስችል ፕሮጀክት ነው። ሌሎች አገራትም ከውሃ በታች ላለ ሀብት ጥበቃ ሊያውሉት ይችላሉ።
በውሃ አካላት ጥናት ከ20 ዓመታት በላይ ተሞክሮ ያላት ሲሆን፣ ሳይንስን መሠረት ያደረገ ጥበቃ እና መልሶ ማገገም ላይ ትሠራለች።
ሥራው ብዙ ስለሆነ ሁሉም ብቻውን ከሠራ አያልቅም። ሰዎች ተባብረው ዕውቀት እየተጋሩ እየሠሩ ነው። እኔም የድርሻዬን ተፈጥሯዊ ቦታ እንዲያገግም በማድረግ ለእጽዋት እና ማኅበረሰቡ እሠራለሁ።
ሊያን ከሊን-አንስወርዝ
ግላዲስ ካሌማ-ዚኩሶሳ, ኡጋንዳ
የእንስሳት ሐኪም
ሽልማቶች ያገኘች የእንስሳት ሐኪም እና የተፈጥሮ ጥበቃ ባለሙያ ናት። በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ መኖሪያቸው እየጠፋ በመሆኑ አደጋ ውስጥ የወደቁ የተራራ ጎሪላዎችን ለመታደግ ትሠራለች።
ኮንሰርቬሽን ስሩ ፐብሊክ ኸልዝ' የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋ ድርጅት አላት። ሰዎችን እንዲሁም ጎሪላዎች እና ሌሎች የዱር እንስሳት ጤናቸው እና አካባቢያቸው ተጠብቆ አብረው እንዲኖሩ እንዲሁም ብዝኃ ሕይወት እንዲጠበቅ የሚሠራ ተቋም ነው።
300 የነበሩ ጎሪላዎች 500 እንዲደርሱ በሦስት አሥርታት ውስጥ ሠርታለች። እንስሳቱ እጅግ አደጋ ውስጥ ከገቡ ዝርዝር ወደ አደጋ ያጠላባቸው ዝርዝር ተሸጋግረዋል።
በ2021 'ቻምፒዮን ኦፍ ዘ ኧርዝ' በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ተሸልማለች።
የአየር ንብረት ለውጥ በአፋጣኝ መፍትሄ የሚሻ መሆኑ እና የበለጠ ዕውቅና እየተሰጠው መምጣቱ ተስፋ ይሰጠኛል። ቀውሱን ለማስወገድ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፈጠራ መንገዶች አሉ።
ግላዲስ ካሌማ-ዚኩሶሳ
ሶኒያ ካስነር, አሜሪካ
ሰደድ እሳት የሚለይ መሣሪያ ፈጣሪ
በዓለም ግዙፍ ደኖች ውስጥ ሰደድ እሳት የተበራከተበት ዓመት ነው። የእሳት አደጋ ተከላካዮችም አደጋውን ለመቆጣጠር ተቸግረዋል። ሶኒያ ሰደድ እሳትን ቀድሞ የሚለይ መሣሪያ ሠርታለች።
ፓኖ ኤአይ የሚባለው መሣሪያ አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ በመጠቀም ሰደድ እሳት ከመስፋፋቱ በፊት ይጠቁማል። ይህን የሚያደርገው መሬት ላይ ምልክቶች በማሰስ እና ለእሳት አደጋ ተከላካዮች መረጃ በመስጠት ነው። ሕዝቡ መረጃውን እንዲቀባበልም ያደርጋል።
ሶኒያ ከአሥር ዓመት በላይ በተለያዩ የቴክኖሎጂ ተቋማት ሠርታለች።
አስደናቂው የሰው ልጆች ፈጠራ ተስፋ ይሰጠኛል። የቴክኖሎጂና ዳታ መር አሠራር የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ቀውስ ለመፍታት ያለውን ጥቅም አይቻለሁ።
ሶኒያ ካስነር
ኩዩን ዉ, ሲንጋፖር
ታሪክ ነጋሪ
ኩዩን ዉ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች እና በማኅበራዊ ሚዲያ የአየር ንብረት ለውጥ ግንዛቤ የሚሰጡ መሰናዶዎች አዘጋጅ ናት።
የበይነ መረብ ገጿ 'ዘ ዊርድ ኤንድ ዘ ዋይልድ' ይባላል። የአካባቢ ጥበቃ ሳይንስ ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች እንዲስፋፋ ይሠራል። ይዘቶቹ የሚያስተምሩ፣ የሚሞግቱ እና ማኅበረሰቡ የለውጥ አካል እንዲሆን የሚያነሳሱ ናቸው።
በደቡብ ምሥራቅ እስያ የአየር ንብረት ለውጥ ስላስከተለው ጉዳት የሚያወሳ ፖድካስት አጋር አዘጋጅ ናት። ቺዝኬን ይባላል ፖድካስቱ። ከባድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮችን ለመገንዘብ በሚቻል መንገድ ይተነትናል።
የናሽናል ጂኦግራፊክ ወጣት አሳሽም ናት።
የአየር ንብረት ለውጥ ውስብስብ እና አስፈሪ ነው። በፍርሃት ሳይሆን ጠንካራ፣ ነገር ግን ስሱ በሆነ መንገድ ነው ልናየው የሚገባው። ልባችን ለዓለም ግድ ሊኖረው ይገባል። የማይሠራውን አስወግደን የሚሠራውን ማስቀጠል አለብን።
ኩዩን ዉ
ኢልሀም ዩሴፊን, አሜሪካ/ኢራን
የአየር ንብረት እና የአካል ጉዳት አማካሪ
ዐይነ ስውር ጠበቃ የሆነችው ኤልሀም ዩሴፊን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የአካል ጉዳተኞችን እንዲካተቱ ጥረት አድርጋለች። በዋናነት የምታተኩረው አስቸኳይ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ሲገጥም በሚሰጡ ምላሾች ላይ ነው።
ተወልዳ ያደገችው በኢራን ሲሆን ወደ አሜሪካ በ2016 (እአአ) ተጓዘች። በዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መድረክ ላይ ቁልፍ ሚና ትጫወታለች። ኢንተርናሽናል ዲሴብሊቲ አሊያንስ የተባለው ተቋም 1100 አካል ጉዳተኞችን ይወክላል።
ውሳኔ ሰጪዎች ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከአካል ጉዳተኞች ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲገነዘቡ ማድረግ ትኩረቷ ነው። አካል ጉዳተኞች የካርበን ልቀትን በመቆጣጠር እና የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ያላቸውን ሚና ትደግፋለች።
እኛ አካል ጉዳተኞች መፍትሄ ያለ በማይመስል ወቅት ሳይቀር መፍትሄ በማግኘት በተደጋጋሚ ተመስክሮልናል። አካል ጉዳተኞች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል መቆም አለባቸው፤ ይችላሉም።
ኢልሀም ዩሴፊን
ኢዛቤላ ዱልዚክ, ፖላንድ
የድምጽ ባለሙያ
ኢዛቤላ ድምጽ መቅጃ ይዛ ነው የምትጓጓዘው። በአውሮፓ ጥንታዊ የሆነው እና በፖላንድ የሚገኘው ቢሎዊዛ ደን ውስጥ ድምጾች ትቀዳለች።
ሙያው በወንዶች የተሞላ መሆኑ ወጣቷን ሴት ባለሙያ የተለየች ያደርጋታል። ዐይነ ስውር መሆኗም ሌላው ልዩ የሚያደርጋት ነገር ነው።
በ12 ዓመቷ ቤተሰቦቿ ድምጽ መቅጃ ከተጧት ጊዜ ጀምሮ ለድምጽ እና ለብዝኃ ሕይወት ልዩ ትኩረት አላት። በድምጽ ብቻ የነፍሳትን ዝርያ መለየት ትችላለች።
ተፈጥሮ ያሏትን ውብ ድምጾች ለሁሉም ሰዎች ያለ ልዩነት ማጋራት መቻል መታደል ነው ትላለች።
ካናን ዳግዴቪሬን, ቱርክ
ሳይንቲስት እና የፈጠራ ባለሙያ
በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት (ኤምአይቲ) ተባባሪ ፕሮፌሰር ናት። እንደ ጡት ማስያዣ ሊለበስ የሚችል የአልትራሳውንድ መመርመሪያ መሣሪያ በመሥራት የጡት ካንሰርን ቀድሞ መመርመር እንዲቻል አድርጋለች።
አክስቷ በ49 ዓመታቸው ነው ካንሰር እንዳለባቸው እና ካንሰሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ የተነገራቸው። በየጊዜው ምርመራ ቢያደርጉም ሕመሙ ሳይታወቅ ስር ሰዶ ከስድስት ወራት በኋላ ሞተዋል።
በጡር ማስያዣ ውስጥ ገብቶ የጡር ካንሰርን በየጊዜው መመርመር የሚችል መሣሪያ ለመሥራት የተነሳሳችው በአክስቷ ምክንያት ነው። ለጡት ካንሰር ተጋላጭ የሆኑን ለመታደግ የሚውለው ይህ ቴክኖሎጂ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴቶችን ሕይወት ይታደጋል።
ትምኒት ገብሩ, አሜሪካ
የኤአይ ባለሙያ
ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ የአርቴፍሻል ኢንተለጀንስ ባለሙያ ናት። ኮምፒውተር ሳይንቲስቷ ትምኒት የ'ዲስትሪብዩትድ አርቴፍሻለ ኢንተለጀንስ ሪሰርች ኢንስቲትዩት' ዋና ሥራ አስኪያጅ ናት። ገለልተኛ፣ ማኅበረሰብ ላይ ያተኮረ፣ ከግዙፍ ቴክኖሎጂ ተቋማት ነጻ የሆነ ተቋም ነው።
በፌሻል ሪኮግኒሽን (የፊት ገጽታን በመለየት) ያለውን የዘር መድልዎ በመተቸት ትታወቃለች። ጥቁሮች በኤአይ እንዲካተቱ የሚያደርጉ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች አጋር መሥራች ናት።
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ትምኒት አዲስኮደር ውስጥ የቦርድ አባል ናት። ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ፕሮግራሚንግ ያስተምራል።
በጉግል የኤአይ ሥነ ምግባር ክፍል ውስጥ በአመራር ዘርፍ ትሠራ ነበር። በ2020 በኤአይ የቋንቋ ሞዴል ላይ ጥያቄ ያነሳ ጥናት ከአጋሮቿ ጋር ሠርታለች። ጥናቱ አነስተኛ እና የተገለሉ ማኅበረሰቦች የሚደርስባቸውን መገለል ያሳያል።
በዚህ ጥናት የተነሳ ከጉግል ወጥታለች። ጉግል ጥናቱ ጠቃሚ መረጃን ቸል ያለ ነው በሚል ትምኒት ሥራ ለቃለች ቢልም እሷ ግን መባረሯን ተናግራለች። በሥራ ቦታ ያለው መድልዎም መነጋገሪያ ሆኗል።
ትራን ጋም, ቬትናም
የባዮጋዝ ነጋዴ
በ2012 (እአአ) ትራን አካባቢ የማይበክሉ የኃይል ምንጮችን ለቬትናም አርሶ አደሮች ማስተዋወቅ ጀመረች።
ሁለት ልጆች አሏት። በዚህ ንግድ ያለውን ክፍተት አይታ ነው ወደ ባዮጋዝ ዘርፍ የገባችው። በሃኖይ የጀመረችውን ሥራ ኋላ ላይ ወደ ሦስት አጎራባች አካባቢዎች አስፋፍታለች።
የላም እና የአሳማ እበትን እንዲሁም ሌሎችን ተረፈ ምርቶች በመጠቀም እና ወጪ ቆጣቢ ባዩጋዝ የኃይል ምንጭ አርሶ አደሮች እንዲያገኙ ትሠራለች። እነዚህ ከጋዝ በተሻለ ዘላቂነት ያላቸው ናቸው። ምግብ ለማብሰል እና ለሌላም የቤት ውስጥ አገልግሎት ይውላሉ።
ማኅበረሰቡን የሚያሳትፍ ሥራ በመሥራት እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ፖለቲካዊ ድጋፍ በማስገኘት ትሳተፋለች።
መኖር አለብን። በአግባቡ መኖር አለብን። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ፣ የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ፣ በአግባቡ በመተኛት፣ ተፈጥሯዊ አኗኗር በመከተል የምወዳቸው ሰዎች ጤናቸው እንዲጠበቅ እሠራለሁ። ሰዎች የሚመገቡትን አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያበቅሉና ኬሚካል ያለው ፀረ ተባይ እንዳይጠቀሙ እመክራለሁ።
ትራን ጋም
ክላውዲያ ጎልዲን, አሜሪካ
ኢኮኖሚስት እና የኖቤል ተሸላሚ
ኢኮኖሚስት እና በአሜሪካ የምጣኔ ሀብት ታሪክ አጥኝ ናት። ሴቶችን በሥራ መስኮች በማሰማራት እና የክፍያ ልዩነትን በማጥብበ ረገድ ባከናወነችው ሥራ በምጣኔ ሀብት የዚህ ዓመት የኖቤል ሽልማት ተበርክቶላታል።
ይህንን ሽልማት ስታገኝ ሦስተኛዋ ሴት ናት። ከወንድ የሥራ አጋሮቻቸው ጋር ሽልማቱን ባለመጋራትም የመጀመሪያዋ ናት።
በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት መምህርት ናት። በገቢ ልዩነት፣ በትምህርት እና ስደት ላይ በሠራቻቸው ጥናቶች ትታወቃለች።
ሴቶች ሥራ እና ቤተሰብን አብሮ ለማስኬድ ባደረጉት ትግል እና የእርግዝና መቆጣጠሪያ በሴቶች ሥራ እና በጋብቻ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ዙሪያ በሠራቻቸው ጥናቶች የበለጠ ትታወቃለች።
ማርሴላ ፈርናንዴዝ, ኮሎምቢያ
የአሰሳ ጉዞ አስጎብኚ
በኮሎምቢያ እየጠፋ የመጣውን ንጹሕ ውሃ ለማኅበረሰቡ በማቅረብ ዘርፍ ነው የተሰማራቸው።
ማርሴላ 'ኩምበርስ ብላንክስ' የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት የመሠረተች ሲሆን፣ እሷ እና የሥራ ባልደረቦቿ ከ14 የበረዶ ግግሮች መካል እንዴት ስድስቱ ብቻ እንደቀሩ የግንዛቤ መስጫ ሥራ ያከናውናሉ።
በሳይንሳዊ አሰሳ፣ ተራራ ወጪዎችን፣ ፎቶ አንሺዎችን፣ ሳይንቲስቶችን እና አርቲስቶችን በማሰባሰብ ነው የምትሠራው። የበረዶ ግግር እንዳይጠፋ የተለያዩ ፈጠራ የታከለባቸው ሥራዎችን ትሠራለች።
ፓዛቦርዶ የተባለ ሌላም ፕሮጀክት ያላት ሲሆን፣ በኮሎምቢያ የ50 ዓመታት ወታደራዊ ግጭት የተጎዱ ማኅበረሰቦች ጋር በመሄድም ትሠራለች።
የበረዶ ግግር ሐዘንን እና ማጣትን እንድረሳ አስተምሮኛል። የበረዶ ግግርን ማጣት ከባድ ነው። አሁንም ግን የድርሻችንን መወጣት እንችላለን።
ማርሴላ ፈርናንዴዝ
100 ሴቶች ምንድን ነው?
የቢቢሲ 100 ሴቶች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ላይ ያተኩራል። በመላው ዓለም ያሉ ሴቶችን ዝርዝር በማሰባሰብ በየዓመቱ የሚዘጋጅ ነው። ዘገባ እና ቃለ ምልልስን ያካትታል። ስለ ሴቶቹ ሕይወት በቢቢሲ ገጾች ዘገባዎች ይቀርባሉ።
የቢቢሲ 100 ሴቶችን በኢንስታግራም እና በፌስቡክ #ቢቢሲ100 ሴቶች በሚል ተከታተሉ።
እንዴት 100 ሴቶች ተመረጡ?
የቢቢሲ 100 ሴቶች ቡድን በጥናት እና ለቢቢሲ ከቋንቋ አገልግሎቶች እንዲሁም ከቢቢሲ ሚዲያ አክሽን ጥቆማ በተሰጠው መሠረት ዝርዝር አዘጋጅቷል።
ዕጩዎች የተመረጡት ባለፉት 12 ወራት ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ሴቶች መካከል ነው። ታሪካቸው አነሳሽ የሆነ እና ለማኅበረሰብ አስተዋጽኦ ያለው ሥራ የሠሩ እንዲሁም የዜና ሽፋን ያገኘ ተግባር ያከናወኑ ይገኙበታል።
የዚህ ዓመት ርዕሰ ጉዳይ የአየር ንብረት ለውጥ እና በመላው ዓለም በሴቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ስለሆነ በዘርፉ ብዙ ባለሙያዎች ስማቸው ተነስቷል። ከእነዚን መካከል 28 የአየር ንብረት እና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ተመርጠዋል።
ከተለያየ የፖለቲካ ዕሳቤ እና ማኅበረሰባዊ ሚና የመጡ ሴቶች ድምጻቸው ተወክሏል። አስተያትን የሚከፋፍሉ የራሳቸውን ለውጥ የፈጠሩም ተካተዋል።
ቀጠናዊ ውክልናም በዝርዝሩ ውስጥ እንዲኖር ተደርጓል። ያለ መድልዎ ነው ዝርዝሩ የተመረጠው። በዚህ ዝርዝር ውስጥ ለመካተት ሁሉም ሴቶች ፈቃዳቸውን ሰጥተዋል።